የመገናኛ ብዙኃን የተረጂነት አስተሳሰብን በመለወጥ ዜጎች ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ተረጂነት ሃገራዊ ክብርንም የሚነካ መሆኑን በማስረዳትና ግንዛቤ በመፍጠር በኩል ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎባችኋል-

ሰላማዊት ካሳ- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ ላይ ለሁለት ቀናት የተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት የሰብአዊ ድጋፍ ጠባቂነት አመለካከትን መየቀር ማንም የሚወስደው ኃላፊነት ሳይሆን የመገናኛ ብዙኃንና የኮሙኒኬሽን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ኃላፊነት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም፣ሐብት ያላት ሃገር ናት ያሉት ሰላማዊት ካሳ በየአከባቢው ያሉ የዳበሩ የመረዳዳት ባህሎችን በማጎልበት፣ያለውን ሃብት በትክክል ለይቶ በማወቅ ሊረዳ የሚገባውን ዜጋ በትክክል ሰብአዊ ዕጋፍ እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ መገናኛ ብዙኃን ከአሁን ቀደም ከሚሰሩት ሥራ በበለጠ እና በተለየ አቀራረብ ሊሰሩበት ይገባል፡፡

በተለይ የተሳሳቱ ትርክቶችን በመለወጥ ራሳችንን መርዳት አንችልም፣ከባድ ነው የሚለውን አስተሳሰብ መቀየርና ሕብረተሰቡ ለተግባራዊነቱ እንዲነሳ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ ራስን መርዳት መቻል ያለውን ፋይዳ፣ በአገባቡ መረዳትና ትክክለኛ መልዕክቶችን በመቅረጽ መረጃው ለየትኛው የሕብረተሰብ ክፍል ነው ሊደርስ የሚገባው የሚለውን በአግባቡ ለይቶ ማወቅ፣ለዚህ የሚሆን ትክክለኛ የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ነድፎ መሥራት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ራስን መመገብ አቅም እንዳለ ማሳየት፣ራስን መርዳት ለምን እንደሚያስፈልግ መረዳት የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት ከሚገቡ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ለመገናኛ ብዙኃኑ ባቀረቡት አጭር ገለጻ ላይ አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም (ዶ/ር) በበኩላቸው ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመምራት በጋራ መግባባት መቻል እጅጉን ወሳኝ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የሚዲያው ድርሻ ትልቅ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ዕርዳታ ጠባቂነት ሃገርን እጅ ከወርች አስሮ የሚጥል፤ ዜጎች ለልማት እና ለብልጽግና ያላቸውን ተነሳሽነት የሚገድል በተቃራኒው ጠባቂነትን ወደ አለመግባባትና ጸብ የሚመራ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ተረጂነት እና ጠባቂነት ክብርን ዝቅ የሚያደርግ፤ የሚያዋርድ ነጻነትን የሚጋፋ እና የሚጻረር ብሎም ለዘመናዊ ቀኝ ተገዥነት የሚያጋልጥ ተግባር ስለሆነ ይህን መዋጋት የምንችለው በሀሳብ መግባባት ስንችል ነው ብለዋል።

ተረጂነት የፖለቲካ ጥገኝነት፤ ለልማት እንቅፍት፤ ለሙስና እና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ ተግባር መሆኑን በማንሳት፤ ሰብሰዊ ድጋፍ በራስ አቅም ማለት አስተሳሰብም፤ ተግባርም መሆኑን እና ይሄ ደግሞ ክብርንም ሆነ ሉዋላዊነትን እንደሚያረጋግጥ አመልክተዋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *