የመንግስትና የሲቪክ ማህበራት ትብብር ማጠናከር የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ፣ የልማት ተደራሽነትና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል ጉልህ ሚና እንዳለው የጉራጌ ዞን አስተዳደር ገለጸ ።


በዞኑ የመንግስት፣ የሲቪክ ማህበራትና ድርጅቶች ዓመታዊ የምክክር ፎረም በወልቂጤ ከተማ ተካሄደ።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በምክክር ፎረሙ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በዞኑ የሰፈነው አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ በርካታ ፕሮጀክቶች ወደ ዞኑ እየገቡ ይገኛል።

በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑ በመንግስት እና በሲቪክ ማህበራት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ከፍተኛ እንዲሆን አስችሏቸዋል ብለዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የህብረተሰቡ የልማት ፍላጎት በመንግሥት በጀት ብቻ የማይሟሉ በመሆናቸው ሲቪክ ማህበራትና ህብረተሰቡን በማስተባበር እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ማጠናከር እንደሚገባ አቶ ላጫ አስገንዝበዋል።

ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ዘላቂ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲንከባከባቸው ማድረግ ይገባል።

በዞኑ ለሚገኙ ሲቪክ ማህበራትና አጋር ድርጅቶች መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የገለፁት ዋና አስተዳደሪው ህዝቡ፣ መንግስትና ሲቪክ ማህበራት ፕሮጀክቶቹ ውጤታማ እንዲሆኑ በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዶ ሀሰን በበኩላቸው በዞኑ ሲቪክ ማህበራትና አጋር ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር በመተባበር በርካታ የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

በዞኑ የሚገኙ 27 ድርጅቶች 49 ፕሮጀክቶች በመቅረጽ ወደ ተግባር መግባታቸውን የተናገሩት አቶ አብዶ ለፕሮጀክቶቹ ማስፈፀሚያ ከአንድ ቢሊዮን 328 ሚሊዮን 551 ሺህ ብር በላይ በጀት የተመደበ ሲሆን በጀቱ ለታለመለት አላማ እንዲውል መምሪያው ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

እንደሀገር ብሎም እንደዞን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ ለማድረግ አጋር ድርጅቶች ከመንግስት ጋር ሆነው በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በቀጣይ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተሳትፎ በማጠናከር ህብረተሰቡ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት በልማቱ ላይ መሪ ተዋናይ እንዲሆን እና የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ መስራት ይገባል።

የምክክር ከረሙ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ድርጅቶቹ በተሰማሩባቸው ዘርፎች ላይ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

በቀጣይም መንግስት የሚያደርግላቸው ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በፕሮግራሙ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የስራ ኃላፊዎች፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራት ኃላፊዎችና እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን በስራቸው የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ሲቪክ ማህበራትና ድርጅቶች የማበረታቻ ሰርተፊኬት እና ዋንጫ ተበርክቶላቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *