የመስቃን ወረዳ አስተዳደር የ”ፈራገዘኘ” ባህላዊ ዳኝነት ለሚሰጡ አካላት የምስጋናና እውቅና ፕሮግራም አካሄደ

ጥር 15/2015ዓ.ም

የመስቃን ወረዳ አስተዳደር የ”ፈራገዘኘ” ባህላዊ ዳኝነት ለሚሰጡ አካላት የምስጋናና እውቅና ፕሮግራም አካሄደ

ጥር 14፣ 2015ዓ.ም(ምስራቅ መስቃን ወረዳ መንግስት ኮሚንኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት) የመስቃን ወረዳ አጠቃላይ አመራር ፈራገዘኘ ባህላዊ የዳኝነት ቦታ በመገኘት ዳኝነት ለሚሰጡት አካላት ምስጋናና ስጦታ ማበርከቱ ተገልጿል።

አጠቃላይ የፈራገዘኘ ባህላዊ የዳኝነት ሰነ ሰርዓት የወረዳው ሁሉንም አመራር እና የፈራገዘኘ ሽማግሌዎች በምዕራብ እንቦር ቀበሌ በፈራገዘኘ ቦታ በመገኘት የዳኝነት ሰነ ሰርዓቱ ተከታትለዋል።

የመስቃን ወረዳ ዋና አሰተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሃሰን ከድር በቦታው ተገኝተው እንደተናገሩት የመሰቃን ቤተ ጉራጌ ባህላዊ የዳኝነት ሰርዓት ከወረዳችን አልፎ በተለያዩ ቦታዎች በመምጣት ዳኝነት የሚያገኙበት ትልቅ የባህላዊ ዳኝነት ሰርዓት መሆኑን ገልፀዋል።

አቶ ሃሰን ከድር አያይዘው የፈራገዘኘ ባህላዊ የዳኝነት ሰርዓት ከአካባቢያችን አልፎ በተለያዪ ዞኖችና ክልሎች በመምጣት ፍትሃዊ የሆነ ከምንም ነገር የፀዳ የማንንም የምስከርነት ቃል ሳያሰፈልግ ጥፋተኛው የሆነው ግለሰብ በራሱ አንደበት ጥፋተኝነቱ በመግለፅ

የዳኝነት ውሳኔ የሚሰጥበት ቱባ የመሰቃን ቤተ ጉራጌ ባህላዊ የዳኝነት ሰርዓት እንደሆነ በመግለፅ በቀጣይ ይህንን የፈራገዘኘ የዳኝነት ቦታ ማጠናከር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በእለቱም በፈራገዘኘ ባህላዊ ዳኝነት የሚሰጡ ሽማግልዎችና የፈራገዘኘ ባህላዊ የዳኝነት ቦታ ለማጠናከርና ለመደገፍ ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ አካላት ምስጋናና ስጦታ በዋና አሰተዳዳሪው በአቶ ሃሰን ከድር የተበረከተላቸው መሆኑን ተገልጿል።

ሌላኛው በእለቱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት አቶ አበራ በቀለ በበኩላቸው የፈራገዘኘ የዳኝነት ቦታ ለማጠናከርና ባህሉን ሊገልፁ የሚችሉ የተለያዩ ስራዎች ለመስራት ቀደም ሲል የተጀመረ መሆኑን ተናግርው በተለያየ ችግር ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ስራ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

የፈራገዘኘ የዳኝነት አሰጣጥ :-
በዚህ ሴራ አማካኝነት በአካባቢው ሽማገሌዎች ማለትም ‹‹በማጋዎች››ጉዳዩ ታይቶ የፍርድ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ምናልባት ደግሞ ጉዳያቸው ከማጋዎች በላይ ከሆነ ወደ በላይ ዳኞች እንዲሄዱ ይደረጋል፡፡ እነዚህም ‹‹ራጋዎቹ›› ይባላሉ፡፡

ራጋዎች የሁለተኛ ፍርድ ሰጪ ሽማግሌዎች ሲሆኑ እነዚህም በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ፍርድ ሰጪ አካላት ናቸው፡፡ምናልባትም ጉዳያቸው በራጋ የማያልቅና ቅሬታ ያለው አካል ካለ ወደ መጨረሻው ፍርድ ሰጪ ወደ ሆነው (ገፌቻ) ፈራገዘኘ ያቀናል እነዚህ የሼህ ዑስማን አስረኛው ትውልድ ላይ ያሉ ሲሆኑ የሚኖሩትም ፈራገዘኘ ወይም ምዕራብ ዕምቦር ነው፡፡

በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ /ጎሳዎች/ የነዚህ ትውልድ ሃረጎች ናቸው፡፡
ፍርድ ሰጪዎችም ከጎሳው መሃከል የተመረጡ ሶስት አንጋፋ ራጋዎች ሲሆኑ ፍርድ የሚሰጡት በጎሳው መሃከል ተቀምጠው ነው፡፡ እነሱጋ ፍርድ የሚሰጠው ጥፋተኞቹ በአካባቢያቸው በተመረጡ የጉዳ ሽማግሌዎች ጉዳያቸው አልቆ በመጨረሻ በጉዳ ዳኛቸው አማካኝነት ተያይዘው ከመጡ በኋላ ነው፡፡

እነሱን የሚዳኙ ሰዎች ፍርድ የሚሰጡት እነሱ ባሉበት ፈራገዘኘ መንደር ካልሆነ በስተቀር በምንም አይነት ሌላ ቦታ ተቀምጠው አይወስኑም፣
ለምሳሌ፡- አንድ ሰው የሌላ ሰው ህይወት አውቆም ሆነ ሳያውቅ ቢያጠፋ ከነበረበት መንደር ይሰወራል፡፡

ቤተሰብም ካለው ዘመድ ወዳለበት ስፍራ መንደራቸውን ለቀው ይሄዳሉ በመጨረሻግን ገዳዩ ደም እነዲያልቅለት በመጀመሪያ በአካባቢ ሽማግሌዎች /ማጋ/ እንዲጨረስ ይደረጋል፡፡

ይህም በሚሆንበት ጊዜ ሁለቱም የጉዳ ሽማግሌዎች ይይዛሉ፡፡ የጉዳ ሽማግሌ የሚያስፈልግበት ምክንያት ሁለቱም ወገኖች በተንኮል እንዳይፈላለጉና ቃልኪዳን ማክበራቸውን ይቆጣጠራል፡፡

ምናልባት መሃላው ፈርሶ ድርጊቱ ተፈፅሞ ቢገኝ በራሱም ሆነ በልጅ ልጆቹ ላይ ጥፋት ስለሚደርስ በባህሉ ረገድ በጣም ይፈራል ለጊዜው የመሃላው ተፈፃሚነት ቢዘገይም ከአንድና ከሁለት ትውልድ በኋላ ሊደርስ ስለሚችል ተሳስቶም ቢሆን ላድርግ ቢል ጥሩ አይሆንለትም ገዳዩ ቢኖርም ባይኖርም አባት የልጁን ሀጢያት በእርቅ ማውጣት አለበትማለት ነው፡፡ ምክንያቱም መሃላው ቤተሰብን ጭምር ስለሚመለከት ነው፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ራጋዎች ያገዳደሉን ሁኔታ በደንብ ካጠኑ በኋላ ለተገደለበት አባትና እናትቡሉኮ፣የወተት ላም፣ወይፈን… ወዘተ ይሰጥ ይባላል፡፡

ይህም ‹‹ወርከፈን›› ይሉታል፡፡ ወርከፈን ማለት ካሳ ነው ይህ ሁሉ ከተከናወነ በኋላ የገንዘብ ደም ካሳ ወይም ጉማ እንዲከፈል ይደረጋል ገዳይ የመክፈል አቅም ቢኖረውም ከኪሱ አውጥቶ ብቻውን መክፈል የለበትም

የግድ የእናቱና የአባቱ ወገኖች ባሉበት ቦታ ፈልጎ እየዞረ እርዳታ ጠይቆ ካልሞላለትም ከራሱ ጨምሮ ይከፍላል እግረ መንገዱንም በእጁ የሰው ህይወት ስለማጥፋቱ ራሱን ማጋለጡ ነው፡፡

ስለዚህ እንደዚህ ካላደረገ ደም አልወጣም ወይም ከሃጢያት አልነዓም ማለት ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከተከናወኑ በኋላ ሟች ቤት የገዳዩ ቤተሰቦችና የተገደለባቸው ቤተሰቦች የጉዳ ዳኛ ፊት እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡

ከዚያም ዓይናቸው በነጠላ ይሸፈኑና የእግር አውራ ጣታቸውን ያቀብላሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ፍየል ታርዶ አንጀቱን በማውጣት ዙርያ ቀለበት ሰርተው እንዲታሰሩ ከተደረገ በኋላ
የጉዳ ዳኛው የታሰረውን አንጀት ተራ በተራ ሲቆርጥ እንደዚህ ይቁረጠኝ ብላችሁ ማሉ ብሎ ያስምላቸዋል የተቆረጠው አንጀት ተሰብስቦ እንዲቀበር ይደረጋል ይህም ሁለተኛ መሃላውን አፍርሼ ብገኝ እንደዚህ ልቀበር ማለታቸው ነው፡፡

ይህ ሁሉ ከተከናወነ በኋላ አንዱ የገዳይ ቤተሰብ የሆነች ሴት በሳህን ወተት አድርጋ በእርጥብ ሳር እየነከረች ከውጭ ጀምራ በመርጨት እገዳዩ ቤት ትገባለች የተገደለበትም ቤተሰብ የሆነች እንደዚሁ እያደረገች ትገባለች ይህም ማለት ሰላም ሰፍኖ እርቅ ወርዷል ማለት ነው፣

ቀጥሎ ያለው ማሳረጊያ እንግዲህ የሁለቱም ቤተሰቦች በመሰባሰብ ከብት ይታረድና ፈንጠዝያ ይሆናል እርቅ ወርዶ አንድ ማእድ ላይ ተሰብስበው ከበሉ ቤተሰብ ሆኑ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ከመቀራረባቸው የተነሳ አይጋቡም።
ዘገባው የወረዳው መንግስት ኮሙንኬሽን ፅ/ቤት ነው!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *