የመስቀል በዓል እና ታሪካዊ ዳራ በመምህር ጸዳሉ አባይነህ እይታ


የጉራጌ ሀገረ ስብከት የአዲስ ኪዳንና የቅኔ መምህር ጸዳሉ አባይነህ ከጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ መስቀል በዓል እና ታሪካዊ ዳራው በወፍ በረር እንዲህ አስቃኝተውናል። እናም ያሰናዳነው እነሆ ብለናል።
መስቀል በቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ጊዜ ይጠራል፣ ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል ፣ ብዙ ጊዜ በጸሎታችን፣ በዜማችን፣ በማህሌታችን፣ በአገልግሎታችንና በልዩ ልዩ ነገሮች ሁሉ መስቀል አለ፡፡ መስቀል ማለት ሰቀለ ሰቀለ ከሚል የግህዝ ቃል የተገኘ ሲሆን መስቀል ማለት መስቀያ ተብሎ ይፈታል፡፡
መስቀል የሚለው ቃል ሶስት ፍቾች አሉት እነሱም :አምላካችን መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን ወደዝህ አለም መቶ የተቀበለው መከራ መስቀል ይባላል፡፡
በሌላ በኩል ክርስቲያኖች የእግዚያብሔር ቤተሰቦች በዚህ አለም ሲኖሩ የሚደርስባቸው፣የሚገጥማቸው ፈተና መስቀል ተብሎ ይጠራል፡፡ለዚህም አምላካችን መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር የሚወደኝ ቢኖር መስቀሌን መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ ብሎ አስተምሯል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ መስቀል ራሱ ልዑለ ባህሪ ቅዱስ እግዚያብሔር ከሶስቱ አካል አንዱ አካል የሆነው መድህን አለም እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ተብሎ ይጠራል፡፡

ጸሎትም የሚጀምረው በመስቀሉ አማትበን ነው፣የሚያልቀዉም እንዲሁ ነው፡፡ስለዚህ መስቀል ትልቁ በቤተ ክርስቲያናችን የጦር መሳሪያችን ወይንም ጋሻችን ማለት ነው፡፡ስለዚህ መስቀል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከዘጠኙ ንዑሳን ባእላት አንዱ ነው፡፡
መስቀልን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርሲቲያን እንደምታከብረው አባቶች እንዳስተማሩን ፣እንደነገሩን መስከረም 16 እና 17 ቀን ይከበራል ፡፡ ይህም የሆነበት ታላቅ ምክንያት አለ : አምላካችን መድሀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን ወደዚህ አለም መቶ ነበር፡፡
ወደዚህ አለም ሲመጣ ግን ወደ ወገኖቹ መጣ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም እንደተባለው ሁሉ ክርስቶስን ሰቅልው፣ገርፈው፣ሀሞት አጠጥተው ገለውታል፡፡ገለው ብቻ አልተውትም እንደሚነሳ ስለሚያውቁ መቃብሩን አስጠብቀዋል፣ይህም ብቻ አይደለም ፣መስቀሉ ታአምራትን ሲያደርግ ካዩ በኋላ መስቀሉ ህሙማንን ሲፈውስ፣ ሙታንን ሲያስነሳ ፣ለምጽን ሲያነጻ፣ ዱዳ የሆነውን ሲያናግርና ልዩ ልዩ ታአምራትን ሲያደርግ ስለተመለከቱ አይሁድ በምቀኝነት ተነሱ ማለት ነው፡፡ትልቁ መስቀል በዓል የሚከበርበት ምክንያት ይህ ነው፡፡
አይሁድ ክርስቶስን እንደስቀሉት ሁሉ እንደገና ደግሞ መስቀሉንም ተአምር እያደረገ ነው ተባለና የክርስቶስን መስቀል ተቀበር፡፡ወዲያውኑ ተቀብሮ በዚያን ቦታ 300 መቶ ዘመን ያህል ቆየ ማለት ነው፡፡እንዲህ ሲቆየ በአከባቢው የሚኖሩ ክርስቲያኖች በየሩሳሌም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ተማርከው ነበር፡፡እየሩሳልም ፈርሶ ስለነበር እነርሱም መስቀሉን ሊያገኙ አልቻሉም፡፡
በአካባቢው የሚኖሩ ማህበረሰቦችም ልጆቻቸው ሲታመሙ ፣ ሲሞቱ መስቀል ያድንልናል ብለው ሲሄዱ መስቀሉ ተቀብሯል ፡፡በዚያ በቦታው ግን የሌላ ሰው መስቀል ተራ መስቀል አስቀምጠው ነበር፡፡መስቀሉን ሲቀብሩት አይሁዶች ዘጠኝ ክንድ ወደታች ጥልቀት ቆፍረው ከላይ ድንጋ ከታች ድንጋ አድርገው ሶስት መስቀል ቀበሩ፡፡በመሀል የክርስቶስ፣በቀኝ የጥጦስ ፣በግራ የዳቅርሳ አድርገው ቀበሩት፡፡
በአካባቢው ያሉ ሰዎችም መዳን አልቻሉም፡፡መስቀሉ የት ሄደ እያሉ ወደ እግዚአብሔር ያለቅሱ ጀመሩ፡፡ እግዚአብሄርም ስራውን ያለ ምክኒያት ስለ ማይስራ ወዲያውኑ እሌኒና ተርቢኒዎስ የሚባሉ ሰዎች ለዚህ መስቀል መውጣት ምክንያት ሆነዋል፡፡እሌኒና ተርቢኒዎስ ባልና ሚስት ሲሆኑ የሚተማመኑና የሚስማሙ ነበሩ፡፡
ተርቢኒዎስ የሚተዳደረው በንግድ ነበር፡፡ አከባቢውን ለቆ ወደ ሌላ ቦታ ለንግድ ሄደ ፡፡ሄዶም ሲመለስ በአካባቢው ባህር ይበዛል፡፡ከባህር ሲደርሱ ተሻገሩና ጓደኞቹ ባህሩን በስላም ተሻገርን እግዚያብሔር ይመስግን፤ ነገር ግን ሚስቶቻችን ሰው ሳይለምዱ ሰው ሳይወዱ ብናገኝ እንዴት ደስ ባለን ነበር ብለው ሀሳብ አቀረቡ፡፡
ይህን ጊዜ ሁሉም ሚስቶቻቸውን ሲጠረጥሩ ተርቢኒዎስ የኔ ሚስት በፍጹም አታደርገውም የሚል ሀሳብ አነሳ። ያንተ ሚስት ከሴቶቹ ወገን አይደለችምን? የሄዋን ልጅ አይደለችምን? እነሱ ጊዜ ካገኙ ከተመቻቸላቸው ለዚህ መቼ ይጨነቃሉ ብለው ሀሳብ ሲያቀርቡለት በፍጹም አይሆንም አለ ፡፡ ወዲያውኑ ተወራረዱ በል እንግዲያስ እኔ ሄጄ ለምጃት ለምዳኝ ብመጣ ምን ትሰጠኛለህ ብሎ ጠየቀው፡፡ እስካሁን የደከምኩበትን እሰጥሐለው ከለመደችህ ከለመድካት ተባብለው ተወራረዱና ሄደ፡፡
ያ ሰው ያቺን ሴት የሚያገኝበትን ምክኒያት ፈለገ፣ ከብዙ ምክኒያቶች በኋላ በመጨረሻ እሌኒ ልትታጠብ አትክልት ቦታ እንደወጣች እንደ እንቁ የሚያበራ ሀብል ነበር ፤ይህንን አገልጋዩዋ በድብቅ ገንዘብ ተቀብላ አሳልፋ ሰጠችው። ይህንን ተቀብሎ ሄደና አሳየው በጣም አዘነ 06 አመት የደከመበትን ለሱ ሰጠውና ወደ ቤቱ ሄደና ሰላም አላላትም ከዚያ እሷ ምን ሆነህ ነው ቀድሞ ትወደኝ ነበረ ቀድሞ እንኳን አንደ ቀን ሁለት ቀን በወጣህ ጊዜ እናፍቅህ ነበር፡፡
አሁን ግን ቸል ብለኸኛል ምንድ ነው ችግሩ ስትለው፤እኔማ እስካሁን የደከምኩበትን ገንዘቤን ማእበል በላብኝ አላት፡፡አንተን እንኩዋን አልወሰደህ እንጂ ምን ችግር አለው ቢበላው ለፍተን ደክመን እናገኛዋለን የሚል ሀሳብ አቀረበችለት፡፡ከዚያን ወዲያውኑ ምን አለ አበድሬ በኖርኩበት ሀገር ተበድሬ፣ ሰጥቼ በኖርኩበት ሀገር ተሰጥቼ፣ተከብሬ በኖርኩበት ሀገር ተዋርጄ አልኖርም እሄዳለሁ ብሎ ሲነሳ ባልና ሚስት አንድ አካል ስለሆኑ በደስታው ጊዜ አብሬው ኖሬያለሁ ፤አሁንም በመከራህ ጊዜ አልለይህም ብላ ተከተለችውና ከባህር አጠገብ ሲደርሱ ወዲያውኑ እሌኒ እኔ ሳምንሽ ከድተሽኛል ስወድሽ ጠልተሽኛል ከኔ ሌላ ሰው ለምደሻል አለና ነገራት፡፡
እኔ አንተን ትቼ ማንን ወድጄ አንተን አርቄ ማንን አቅርቤ የሚል ሀሳብ ስታቀርብለት ፤በፍጹም አለና ያንን ሀብል አሳያት፡፡ ደነገጠች በፍጹም ይኸው እግዚያብሔርን እኔ አላደረኩም ብላ እሷ ማለችለት፡፡እሱም ካደረግሽው ስራሽ ያጥፋሽ ካላደረግሽው ስራሽ ያውጣሽ አለና በሳጥን አድርጎ ባህር ላይ ጣላት፡፡ይህ ዉኃ ወስዶ አንድ አከባቢ ጣላት፡፡ ቁንስጣ የሚባል ንጉስ አገኛትና ለ40 ቀን ያህል አብረው ከቆዩ በኋላ በጣም ቆንጆ ስለነበረች ሚስቱ አደረጋት፡፡
ከዚያን በኋላ ቆስጣንጥኒዎስ የሚባል ልጅ ወለደች እሱ አርመናዊ እሷ ደግሞ ክርስቲያን ነበርች፡፡የሃይማኖት ትምህርት እያስተማረችው ካሳደገችው በኋላ የእግዚአብሔር ጊዜው ሲደርስ ይህ ሰው ገና በ18 ዓመቱ ሮማውያንን እንዲመራ እድል ተሰጠው ፡፡ሮምን ሲመራ ለቤተክርስቲያን ታላቅ አገልግሎቶችን ፈጽሟል፡፡
ንግስት እሌኒም ይህንን ከተመለከተች በኋላ የክርስቶስ መስቀል እንደተቀበር፣እውነት እንደጠፋ፣ሐሰት እንደነገስ፣ብርሃን እንደተቀበር፣ ጨለማው እንደወጣ ይህንን መቼ ይሆን የሚሳካልኝ እያለች ታስብ ነበር፡፡ከእለታት አንድ ቀን ለቆስጣንጥኒዎስ ለልጅዋ አቀረበችለት፡፡እሱም ወዲያውኑ ሀሳቡን ተቀበለና 326 ዓመተ ምህረት እናታችን ቅድስት እሌኒ ሰራዊቷን አስከትላ መስቀሉን ለማውጣት መስከረም 17 ቀን ቁፋሮ አስጀመረች ፡፡
ይህ ቁፋሮ ሲጀመር ቦታውን ለማገኘት ብዙ መከራ አይታለች፡፡ አይሁድ ቆሻሻ ሌላ ቦታ እንዳይደፋ መክረው ስለነበር ያ ቆሻሻ እንደ ተራራ አድጎ ስለ ነበር ማወቅ አልተቻለም ነበር፡፡ መስቀሉ ያለበትን ቦታ ለማወቅ የሆነ ዘዴ ተጠቀመች ኪራቆስ የሚባል ሰው አገኘች፡፡ይህ ኪራቆስ የሚባል ሰው መስቀሉ ያለበትን ቦታ እንዲነግራት ጨው የበዛበትን ምግብ አበላችውና ውኃ ከለከለችው መስቀሉ ያለበትን ቦታ ካልነገርከኝ ውኃ አልሰጥህም አለችው፡፡
ውኃ ጥሙ ሲጠናበት ሊሞት ሲል ውኃ ከሰጠሸኝ አሳይሻለው የሚል ሀሳብ ሰጣት ፡፡ ወዲያውኑ እንዲነግራት ጠየቀችዉ እሱም እኔ ትክክለኛ ቦታዉን አላቅም፡፡ ሶስት ተራሮች አሉ። ከነዚህ ተራሮች አንዱ ሊሆን ስለሚችል በይ እጣን እጠኚና ቦታውን ታገኚዋለሽ አላት፡፡ይህንን ሀሳብ ተቀበለችና እናታችን ቅድስት ንግስት እሌኒ ወዲያውኑ እጣን ማጨስ ጀመረች ከዚያም እጣኑ ከሶስቱ ተራራ በአንዱ ላይ ሰማይ ደረሰና ወደ ምድር መጣ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው አለችና ወዲያውኑ በዚህ ተራራ ላይ ሰራዊቷን አስከትላ መስከረም 17 ቀን ቁፋሮ አስጀምራ እስከ መጋቢት 10 ቀን የአምላካችን የመድሃኒታችን የእየሱስ ክርስቶስ መስቀልን አግኝታዋለች ፡፡
በዚህን ዕለት መቃሪዎስ የሚባለውን የእየሩሳሌምን ሊቀ ጳጳስ ጠርታ እናታችን ቅድስት እሌኒ በዓሉን አክብራለች ማልት ነው፡፡ በዓሉ መጋቢት 10 ቀን ነበር የሚከበረው ለምን ቢባል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን 7 አጹዋማት አሉ። ከነዚህም አፅዋማት መካከል ታላቁ ጾም አብይ ጾም መጋቢት ላይ ይውላል፡፡መጋቢት በጾም በዓል ማክበር ስለማይቻል በዚህ ሃሳብ ሊቃውንት ተስማምተው መስከረም 17 በዓለ መስቀሉን እናከብራልን ማለት ነው፡፡ስለዚህ መስከረም 17 ቁፋሮ የተጀመረበትና የመስቀል ቤተ ክርስቲያን የታነጸበት መስቀል ወደ ቤተ ክርስቲያን የገባበት መሆኑን ቅዱሳን መጻህፍት ይነግሩናል ማለት ነው፡፡በዓሉን ስናከብር በመረዳዳት፣ በመደጋገፍና በመቻቻል እንዲሆን መልእክታቸውን መምህር ጸዳሉ አባይነህ አስተላልፈዋል።
ያዘጋጀው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *