የመስቀል በዓል ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበርና የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በቅንጅት መሰራት እንዳለበት ተገለጸ።

መስከረም 9/2015 ዓ.ም

የመስቀል በዓል ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበርና የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በቅንጅት መሰራት እንዳለበት ተገለጸ።

የመስቀል በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅና የመንገድ የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ከሁሉም ወረዳዎችና ከተማ መስተዳድሮች የተዉጣጡ የሰላምና ጸጥታና የሚሊሻ ጽህፈት ቤት ሀላፊዎች ፣ የፖሊስ አካላት ፣የመንገድና ትራንስፖርት ኃላፊዎችና የክልሉ ኮማንድ ፖስት አካላት በወልቂጤ ከተማ የምክክር መድረክ አካሄደዋል።

በምክክር መድረኩ የተገኙት የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አበራ ወንድሙ እንዳሉት በዞኑ በዋናነት ከሚከበሩ በአላት መካከል የመስቀል በአል አንዱ ነዉ።

በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የአካባቢዉ ተወላጅ የእምነቱ ተከታዮችና ሌሎችም እንግዶች የመስቀል በዓል ለማክበር ወደ ዞኑ በብዛት ይመጣሉ ብለዉ በአሉን ካለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲያከብሩ የሚመለከታቸዉ አካላት በቅንጅት መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የመስቀል በዓል ባህላዊ ዕሴቱን ጠብቆ ለማክበርና የትራፊክ አደጋ ለመከላከልና የመንገድ ደህንነት ፣ ፖሊስ ፣ የትራፊክ አካላትና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተቀናጅተዉ መስራት እንዳለባቸዉም አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሀላፊ ተወካይ እና የዞኑ ሚሊሻ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብድል ሀፊዝ ሁሴን እንዳሉት ህግ ለማስከበር የጽታ ስጋት የሆኑ ቦታዎችን በመለየት ወደ ተግባር መገባት አለበት ብለዋል።

መጪዉ የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚኖሩ የዞኑ ተወላጆች ወደ ትዉልድ ቀያቸዉ በዓል ሊያከብሩ እንደሚመጡና በዓሉ በሰላም አክብረዉ ወደ መጡበት አካባቢ እስኪመለሱ ድረስ ሰላምና ጸጥታዉ የማስከበር ስራዉ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሁሉም አካባቢዎች የሮንድ ስራዉ አጠናክሮ በማስቀጠል በዘላቂነት ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባም ጥሪ ያቀረቡት አቶ አብድልሀፊዝ የጸረ ሰላም ሀይሎች እንቅስቃሴ በንቃት በመከላከል የተጀመረዉን ህግ የማስከበሩ ስራ ከመቼዉም ጊዜ በትኩረት ይሰራል።

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ የመንገድ ደህንነት አስተባባሪ አቶ ቅባቱ በረዳ በበኩላቸዉ ባለፉት አመታት በተከናወኑ የበዓላት ወቅቶች የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠልና ክፍተቶች በማረም በመንገድ ልማትና ቁጥጥር ስራዉ አጠናክሮ መስራት ይገባል።

በመስቀል በአል የመንገድ ትራፊክ አደጋ መቀነስ እንዲያስችል ሁሉም በቅንጅት መስራት እንዳለበትም አብራርተዉ የፖሊስ አባላት በመናኸሪያ ግቢ ዉስጥ በአሉ እስኪያልፍና የተሽከርካሪ ፍሰት እስኪቀንስ በቋሚነት ተተክለዉ መስራት እንዳለባቸዉም ጠቁመዋል።

የተሻለ የትራንስፖርት ፍሰት እንዲኖርና የቁጥጥር ስራዉን ከበዓል በፊት አደጋ እንዳይከሰት የግንዛቤ ስራ በስፋት መሰራት እንዳለበተም አመላክተዋል።

በምክክር መድረኩ የተገኙ አንዳንድ ባለድርሻ አካላቶች በሰጡት አስተያየት ለጸጥታ ስጋት የሆኑ ቀጠናዎችን በመለየትና ሰርጎ ገቦቹን ለመከላከል በቅንጅት እየሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል።

የመስቀል በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅና የትራፊክ ፍሰት ለመቀነስ እንዲሁም አደጋ እንዳይፈጠር ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም አብራርተዋል።

በምክክር መድረኩ ከሁሉም ወረዳዎችና ከተማ መስተዳድሮች የተዉጣጡ የሰላምና ጸጥታና የሚሊሻ ጽህፈት ቤት ሀላፊዎች ፣ የፖሊስ አካላት ፣የመንገድና ትራንስፖርት ሀላፊዎችና የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላቶች እንዲሁም የክልሉ ኮማንድ ፖስት አካላት ተሳትፈዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *