የመረጃ ጥራትና ወቅታዊነት በማረጋገጥ ህዝቡ በዘላቂነት በልማቱ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ፕላንና ልማት መምሪያ አስታወቀ።

በጉራጌ ዞን ፕላንና ልማት መምሪያ ለ2016 በጀት ዓመት ሀብት ማከፋፈያ የሚዉል በቀመር መረጃ ዙሪያ ለዞን ፣ለወረዳና ከተማ አስተዳድር አመራር ፣ባለሙያ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላቶች ጋር ዉይይት በወልቂጤ ከተማ ተካሄዷል።

የጉራጌ ዞን ፕላንና ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ከበደ ሀይሌ እንዳሉት የቀመር ፍትሃዊነት በዋናነት ሊረጋገጥ የሚችለዉ የጠራና ወቅታዊነት ያለዉ መረጃ በማሰባሰብ በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ እንዲዉል ማድረግ ነዉ።

በአንዳንድ ወረዳዎች አካባቢ ትክክለኛ መረጃ ከማድረስ ጋር የሚታዩ ችግሮች በተገቢዉ በመቅረፍ በዘርፉ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚገባም አስታዉቀዋል።

የመረጃ ጥራትና ወቅታዊነት በማረጋገጥ የቀመር ፍትሃዊነት ማረጋገጥ ይገባል ያሉት አቶ ከበደ የህዝቡ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጀት በፍትሃዊነት ማግኘት እንደሆነም ጠቁመዋል።

ቀደም ሲል እንደ ዞን የቀመር ችግር አለ በሚል ይነሱ የነበሩ ክፍተቶች በስፋት ይገመገም እንደነበረ አስታዉሰዉ ይህንንም ለማጥራት የፊት አመራሩና የሚመለከታቸዉ የዘርፉ ባለድርሻ አካላቶች በትኩረት እየሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል።

ሌላዉ እንደ ችግር ይነሳ የነበረዉ የቆዳ ስፋት ችግር ሲሆን በዚህም በሶዶ ወረዳ 3 ቀበሌዎች ማለትም በኦሮሚያ ክልል ይተዳደሩ የነበረና አሁን ላይ በዞኑ ስር የተካተቱበት እንደሆነም የጠቆሙት ሀላፊዉ የዞኑ የቆዳ ስፋት 5 ሺህ 9 መቶ 60 ካሬ ኪሎ ሜትር እንዲሆን የማድረግ ስራ መስራታቸዉም አመላክተዋል።

ከቆዳ ስፋት ጋር ተያይዞ ሌሎች ቀሪ ስራዎችም መኖራቸዉ የጠቆሙት አቶ ከበደ ማሮቆ ዌዳ ላይ አንድ ቀበሌ እንዳለም አመላክተዉ ይህንንም ለማስገባት መረጃ የማደራጀት ስራ እየሰሩ እንደሆነም አብራርተዋል።

ከእንስሳት ቁጥር ፣ ከሰብል ምርት ፣ከከተማ ልማት ፣ ከጤና ተቋም ፣ ከጤና ባለሙያ ፣ ከትምህርት ጥራት ፣ከትምህርት ቤቶች ቁጥርና የተማሪዎችና የክፍል ጥምርታ ከነዚህ ጋር ተያይዞ የመረጃ ክፍተቶች መኖራቸዉም አስረድተዋል።

ይህንንም ለማጥራት ከክልል ፣ከዞን እንዲሁም በወረዳ ደረጃ ያለዉ የመረጃ ልዩነት የማጥራት ስራ በመስራት ለወረዳ አስተዳዳሪዎችና ለመድረኩ ተሳታፊዎች ጭምር የተሰጠበት ሁኔታ መኖረም ጠቁመዉ ይህንንም በ5 ቀን ዉስጥ ያሉ ልዩነቶች በማጥበብ ዞኑ በፍትሃዊነት በጀት ሊያገኝ የሚችልበት መንገድ መፍጠር እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመድረኩ የተገኙት የጉራጌ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ክብሩ ፈቀደ እንዳሉት የፕላንና ልማት ተቋም እየሰራቸዉ ያሉ ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ለዉጥ እየመጣ እንደሆነም ተናግረዋል።

የህዝብ ተጠቃሚነት በተገቢዉ ለማረጋገጥና በዘርፉ ዉጤታማ ስራ ለመስራት የመረጃ ጥራትና ወቅታዊነት ላይ ትኩረት አድርጎ መሰራት አለበት ብለዋል።

የሚነሱ የመልካም አስተዳድር ችግሮች ፣በየደረጃዎ ህዝቡ የሚያነሳዉ የልማት ጥያቄዎች በበጀት አስደግፎ መመለስ ግድ የሚል እንደሆነም አመላክተዉ ተቋሙን ከሌላዉ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ መደገፍ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የዞኑ ህዝብ በልማት ተጠቃሚ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ባለድርሻ አካላቶች ከመቼዉም ጊዜ በላይ ተቀናጅተዉ መስራት እንዳለባቸዉም አስረድተዋል።

በመድረኩ የተገኙ አካላቶች በሰጡት አስተያየት ፍትሃዊነት የልማት ተደራሽነት ለማረጋገጥ የመረጃ ጥራትና ተአማኒነት ያለዉ መረጃ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በትምህርት በጤና በመንገድና በሌሎችም መሰረተ ልማት ተጨባጭ ለዉጥ እንዲመጣ እየተሰራ ያለዉ ስራ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመላክተው የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *