የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህልን በማሳደግ በዞኑ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አሳሰበ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ይህን የተናገሩት በጉራጌ ዞን ቀቤና ወረዳ በፈቃዶ ቀበሌ የወይዘሮ ደሶ ስራጅ የቤት ግንባታ ባስጀመሩበት ወቅት ላይ ነው።

እንደ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በዞኑ አቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ በክረምትና በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋውያን ቤት ከመገንባት ባለፈ አዝመራ የመሰብሰብ ስራና ሌሎችም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎችን እየተከናወኑ ነው።

የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ በክረምትና በበጋ የበጎ አድራጎት ስራ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት በክልሉ በሞዴልነት የሚጠቀሱ ሲሆን በዞኑ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ፍትሃዊና ሁሉንም ባካተተ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራው ያለው ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

በዞኑ መሰል ችግር ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት ባለሃብቶች፣ አቅም ያላቸው አርሶ አደሮችና ማህበረሰቡን በማስተባበር ችግር ውስጥ ላሉ የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግና ስራዉ ለማስፋት ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በዛሬው እለት በቀቤና ወረዳው እንደ አዲስ የሚገነባው የወ/ሮ ደሶ ስራጅ ቤት በጥራት በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ የዞኑ አስተዳደር ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አወል ጅማቶ እንደገለጹት በ2014/15 የክረምትና የበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ስራዎች መሰራታቸውና እየተሰራ ይገኛል።

በበጋ የበጎ አድራጎት ስራ ከቤት ግንባታ ባለፈ በርካታ ስራዎችን እየተከናወኑ እንደሚገኝ ጠቁመው ወጣቶችን በማሳተፍ የአፈርና ጥበቃ ስራ ላይ ዉሃ የማጠጣትና እንክብካቤ፣ የደም ልገሳና ሌሎችም ስራዎች እየተከወኑ ይገኛል ብለዋል።

በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶችን በማሳተፍ ከህዝብና ከመንግስት ይወጣ የነበረውን ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን ተችሏል ብለዋል።

በዞኑ በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊሰሩ ከታቀዱ 451 ቤቶች ውስጥ እስካሁን 195 ቤቶችን መገንባት መቻሉን አመላክተዋል።
በክረምትና በበጋ የበጎ አድራጎት ስራ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የወልቂጤ ቀይ መስቀል ማህበር እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ መሰል ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን ካለባቸው ችግር ለማላቀቅ ባለሀብቶች፣ ግብረሰናይ ድርጅቶችና ወጣቶችን በማሳተፍ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

የቀቤና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብደላ ጀማል በበኩላቸው ዞኑ በወረዳው በክረምትና በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቤት መገንባት ብቻ ሳይሆን በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።

በወረዳው በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 34 አዳዲስ ቤቶች መገንባት መቻሉን ጠቁመው በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወይዘሮ ደሶ የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዞኑ ላደረገው በጎ ተግባር አመስግነዋል።

በጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብዶ ድንቁ በዞኑ በክረምት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ 807 ቤቶችን መገንባቱን ጠቁመው በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 451 ቤቶችን በመገንባት ከ2ሺህ 7መቶ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

መምሪያው በዘርፉ በርካታ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ አብዶ በተለይም የዘማች ቤተሰብ መደገፍ፣ የበጋ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠትና ሌሎችም መሰል ስራዎች እየተሰራ ይገኛል።

በዞኑ በ2015 በጀት አመት 2ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ 2ሺህ 4መቶ 47 ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን አመላክተዋል።

የጾም ወቅት ምክንያት በማድረግ ማዕድ ለማጋራት መታቀዱን ያነሱት ኃላፊው ለዚህም ከባለሀብቶች፣ ከበጎፈቃደኞች፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዉ እነዚህና መሰል ስራዎችን በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በበጋ የበጎ አገልግሎት 109ሺህ ወጣቶችን ለማሳተፍ ታቅዶ እስካሁን 89 ሺህ ወጣቶችን ማሳተፋቸውን ገልጸው በቀጣይም ወጣቶችን አልባሌ ቦታ ከመዋል ይልቅ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በቀቤና ወረዳ ፍቃዶ ቀበሌ በዛሬው እለት ቤታቸውን በአዲስ እየተገነባላቸው የሚገኙ ወይዘሮ ደሶ ስራጅ እንዳሉት ከዚህ በፊት በክረምት ወቅት ዝናብና ጎርፍ በበጋ ወቅት ደግሞ ጸሀይና ብርድ ይፈራረቅባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ከነበሩበት ችግር እንዲወጡ መንግስት ስለደረሰላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመው ይህንን ላደረገላቸው ለዞኑ አስተዳደር ምስጋና አቅርበዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *