የመሃል አምባ ኮንስትራክሽንና ኢንደስትሪያል ኮሌጅ ለ2ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 138 ሰልጣኞች በዛሬው ዕለት በታላቅ ድምቀት ማስመረቁ ተገለፀ።


መርሃ ግብሩ በሃይማኖት አባቶች ምርቃት ተጀምሯል።
ዛሬ የተመረቁ ተማሪዎች በቀን፣በማታ እና በቅዳሜና እሁድ መረሃ ግብር ከደረጃ 1እስከ4 ሲሰለጥኑ የቆዩ ናቸው።

የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሚፍታ ሁሴን ለተመራቂ ሰልጣኞችና ቤተሰቦች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን መንግስት ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና አንዱና ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል።

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የስራ ገበያን መሰረት ያደረገ፣ ክህሎት የተላበሰ፣ ተነሳሽነት ያለው፣ በስነ-ምግባሩ ምስጉን የሆነና ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም የሚችል ዜጋ ማፍራት ለአንድ ሃገር እድገትና ብልጽግና ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ ከፍተኛ በጀት በመመደብ፣ ባለሃብቱን፣ በጎ አድራጎት ድርጅቶችንና ህብረተሰቡን በማስተባበር ተግባሩን እያሳለጠው እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የመሃል አምባ ኮንስትራክሽንና ኢንደስትሪያል ኮሌጅን ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ ላደረጉት ልማታዊ ባለሃብት መሃመድ ገረሱ ሀቢብ እና ቤተሰቦቻቸው በወረዳው ህዝብና መንግስት ስም አመስግነዋል።
ተመራቂዎች በስልጠና ቆይታችሁ ያሳያችሁትን ስነ-ምግባርና የቀሰማችሁትን እውቀት በተሰማራችሁበት የስራ መስክ በአገልጋይነት ስሜት፣ በትህትና አገልግሎት በመስጠት አኩሪ ተግባር መፈጸም ይጠበቅባችኋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የመሃል አምባ ኮንስትራክሽንና ኢንደስትሪያል ኮሌጅ ዋና ዲን ተወካይ ወይዘሪት ሰላማዊት ኡርባኖስ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ኮሌጁ በ2009 ዓ.ም በአይ ሲቲ ዘርፍ 36 ሰልጣኞችን ተቀብሎ ትምህርትና ስልጠና የጀመረ ሲሆን በዘንድሮው 2016 ዓ.ም እውቅና ባገኘባቸው በ6 ዲፓርትመንቶች 141 ተማሪዎች ስልጠና እየሰጠ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
አክለውም በ2ኛው ዙር በኮሌጁ ስልጠናቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ወንድ= 26 ሴት=112 በድምሩ 138 ሰልጣኞች በአይሲቲ፣ በጋርመንት፣ በኮንስትራክሽንና ብረታ ብረት መስክ ስልጠናቸውን አጠናቀው ዛሬ ለምረቃ መብቃታቸውን ወይዘሪት ሰላማዊት ኡርባኖስ ገልጸዋል።

የእለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የጉራጌ ዞን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ስርገማ በበኩላቸው የዛሬ ምርቃት 128ኛው የአድዋ ድል በዓል ቀን መሆኑ ልዩ ትርጉም የሚሠጠው መሆኑን ገልጸዋል።
ትምህርትና ስልጠና ለአንድ ሃገር ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ መሳሪያ ይጫወታል።
በእውቀትና በክህሎት የበለጸገ ማህበረሰብ ቴክኖሎጂ የመፍጠርና የመጠቀም ያድጋል ሲሉ የገለፁት አቶ መስፍን ስርገማ የበለፀጉ ሃገሮች ቴክኖሎጂ መጠቀምና መፍጠር በመቻላቸው ለዚህ መብቃት ችለዋልም ብለዋል።

ዛሬ ላይ በሃገራችንና በዞናችን በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተምረው ለራሳቸው ስራ የፈጠሩና ለሌሎች ስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር የቻሉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ የወረዳው አስተዳደር ኮሌጁን በቅርበት በመደገፍ፣ ለሰልጣኝ ሴቶች የቤት ኪራይ ወጪ በመሸፈን ላበረከተው አስተዋፅኦ በዞኑ ቴ/ሙ/ት/ስ/መምሪያ ስም አመስግነው ለተመራቂዎች እና ተመራቂ ቤተሰቦች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ከተመራቂ ሰልጣኞች መካከል ከ1እስከ 3 የወጡት
ሂክማ ካሳ፣ ዛሃራ ወራቄ እና አባስ ርድዋን በሰጡት አስተያየት ለዚህ መብቃታቸው ደስታ ፈጥሮብናል፣ በተሰማራንበት ሙያ ዘርፍ ህብረተሰቡን በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ ነን ያሉት ተመራቂዎቹ ወጣቶች በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም ገብተው ስልጠና በመውሰድ ብቁና የሰለጠነ ዜጋ ከመሆን ጎን ለጎን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በምረቃ ስነ- ስርዓቱ ላይ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የቦርድ ሰብሳቢ ረዳት ፕሮፌሰር አበበ ያበኬር፣ የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ኸይሩ አህመድ፣ የተመራቂ ተማሪ ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የወረዳ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል።
ዘገባው የገ/ጉ/ወ/ወ/መ/ኮ/ጉ/ጽ/ቤት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *