የህብረተሰቡ የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ የአገና ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

መስከረም 10/2015

የህብረተሰቡ የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ የአገና ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

ለከተማው ልማትና እድገት ለማሳደግ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ የአገና ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የአገና ከተማ ከተመሰረተ ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም የመሰረተ ልማት አለመስፋፋትና የከተማው የፈርጅ ለውጥ አለመደረግ የከተማው እድገት አዝጋሚ እንዲሆን አድርገውታል።

ይሁን እንጂ ከተማው ወደ ፈርጅ ሶስት ደረጃ አድጎ በከተማ አስተዳደርነት መተዳደር ሲጀምር መሰረታዊ የህብረተሰቡ ጥያቄዎች የነበሩትን የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታ፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የዲችና ሌሎች መሰል ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ የከተማው ከንቲባ አቶ ሀብቴ ዘርጋ ገልጸዋል።

እንደ ከንቲባው ገለጻ በተጠናቀቀው በጀት አመት 517 ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ 4መቶ ሜትር የዲች ግንባታ እንዲሁም በስምንት መንደሮች የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታ ስራ መስራት ተችሏል።

ከተማው ለነዋሪዎቹ ምቹ ከማድረግ ጎን ለጎን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ሀብቴ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለነዳጅ ማደያ፣ ለሆቴል፣ ለከብት እርባታ እና ለተለያዩ ግልጋሎት የሚውል 10 ሄክታር መሬት ከይገባኛል ነጻ በማድረግ ለኢንቨስትመንት ዝግጁ ማድረግ እንደተቻለ አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም ቦታው ተረክበው ወደ ስራ ያልገቡ ባለሀብቶች በቀጣይ ፍቃድ ባገኙባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ወደ ተግባር መግባት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ህብረተሰቡ የሚጠይቃቸው የልማት ስራዎች ለማከናወን ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ መሰብሰብ ይገባል ያሉት ከንቲባው ግብር ከፋዩ የሚጠበቅበትን ግብር በወቅቱ በመክፈል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

አቶ ሀብቴ ሹሜ እና አቶ ካሳ ኬርጋ የአገና ነዋሪዎች ሲሆኑ ከተማው ራሱን በራሱ ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ አበረታች የሆኑ የልማት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

እንደነዋሪዎቹ ገለጻ በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው የተቀላጠፈ እንዲሆን ረድቷቸዋል ።

በመሆኑም ህብረተሰቡ በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ከተማው ሰላም የሰፈነበትና ስራወዳድ ማህበረሰብ የሚገኝበት አካባቢ በመሆኑ ተመራጭ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎቹ ባለሀብቶች በተዘጋጁ ቦታዎች መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠይቀዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *