የህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

በወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አዘጋጅነት ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የልማት ስራ ጉብኝት ተካሂዷል፡፡

በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በልማት ስራ ጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

በወረዳው 58 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በማኑፋክቸሪን፣ በግብርናና በአገልግሎት ዘርፎች ተሰማርተው የአካባቢው ልማት ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡

በዚህም ከ5 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠራቸውም ባለፈ የወረዳው ገቢ በማሳደግ ከሚመደብለት በጀት 70 ከመቶ የሚሆነውን በራሱ መሸፈን መቻሉን ዋና አስተዳዳሪ ገልጸዋል፡፡

በርካታ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው የተለያዩ የመስኖ ልማቶች ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንስሳት እርባታ ተሰማርተው እራሳቸውንና የአካባቢው ህብረተሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ከማረጋገጣቸውም በተጨማሪ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አቶ ዘውዱ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ዘውዱ ገለጻ ለሰራተኞች ምቹ የስራ አካባቢ እንዲኖር በማሰብ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግባቸው ሁለት ለቢሮ አገልግሎት የሚሰጡ ህንጻዎች አንዱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በዝግጅት ላይ የሚገኝ መሆኑንና የቀሪው ህንጻም ግንባታ እየተፋጠነ ይገኛል፡፡

በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ መልስ በበኩላቸው በመስክ ምልከታው በወረዳው የሚገኙ የተለያዩ የልማት ስራዎች ያሉበት ደረጃ በማየት ጥንካሬያቸውና ጉድለታቸውን በመለየት የሚመለከታው ባለድርሻ አከላት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉላቸው እና መረጃ ለህብረተሰቡ ለመስጠት እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

በልማት ስራ ጉብኝቱ በርካታ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በመስኖ የተለያዩ የልማት ስራዎች በመስራታቸው በሀገሪቱ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት፣ ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠርና ልምዳቸው በማካፈል ሌሎች ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሰሩ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኙ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በመስክ ምልከታው ከታዩ ኢንቨስትመንቶች መካከል የኤማናው ትሬዲንግ አንዱ ነው፡፡ የፋብሪካው ስራአስኪያጅ አቶ አድማሱ ደገሙ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት በማድረግ የተነባበረ ጣውላ እያመረተ መሆኑንና ከ50 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ችለዋል፡፡

ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እንደሚሰራ የገለጹት አቶ አድማሱ የመብራት መቆራረጥ ችግር የሚመለከተው አካል እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል፡፡

በማህበር ተደራጅተው በመሰኖ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ጎመንና የበጋ መስኖ ስንዴ ከሚያመርቱ ወጣቶች መካከል አቶ ጌታቸው ብሩ እንደተናገረው በመስኖ ማምረት ከጀመሩ ወዲህ ከሚያገኙት ገቢ የራሳቸውና የቤተሰባቸውን ኑሮ መምራት ከመቻላቸውም ባለፈ ለሌሎች ወጣቶችም የስራ እድል መፍጠር ችለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *