የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋገጥና ሁለንተናዊ ተጠቃሚ ለማድረግ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን መፍታት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።


የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የግብርና አካላት ግንኙነት አማካሪ ካውንስል የማጠናከሪያ ጠቅላላ ጉባኤ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአረቅጥ ከተማ ተካሄደ።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በወረዳው በግብርናው ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ያለው ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።

በዞኑ የምርምር ማዕከላት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰሩት ያለው ስራ በማጠናከር በግብርናው ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን በዘላቂነት ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

መምሪያው ከመሬት መሸርሸርና ናዳ፣ የግብአት ችግር፣ የፈሳሽ ናይትሮጂንና የዘር እጥረት ችግርና ሌሎችም ለመፍታት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የጉመር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ከድር እንዳሉት በወረዳው በአመት ሶስት ጊዜ በማልማት የአርሶ አደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ማጠናከር ይገባል።

ለዚህም የምርምር ተቋማት የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት ሊያሳድጉ የሚችሉ በምርምር ማዕከላት የተረጋገጡ የምርምር ውጤቶች ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀማመሩ ስራዎችን አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ አንስተዋል።

በወረዳው በግብርናው ዘርፍ የመጣው አበረታች ውጤት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት በተሰራው ስራ መሆኑን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው በዘርፉ ለአርሶ አደሩ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል።

የወልቂጤ የምርምር ማዕከል በወረዳው በኩታ ገጠም የሰራው ስራ ውጤታማ መሆኑና በዚህም አርሶ አደሩ በርካታ ልምድ መውሰዱን ተናግረው እየሰሩት ያለው ተግባር በቀጣይም አጠናክረው እንዲያስቀጥሉም አስገንዝበዋል።

ወረዳው ደጋ እንደመሆኑ መጠን መሬቱ በአሲዳማነት በከፍተኛ ሁኔታ መጠቃቱን ተከትሎ አርሶ አደሩን የመሬቱ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምርና አሲዳማነት ለመቀነስ አርሶ አደሩ መሬቱን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተገቢው በመስራት መንከባከብ እንዳለባቸው ያነሱት አቶ ደሳለኝ የወረዳው መንግስትም እየሰራው ያለው ተግባር አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ገልጸዋል።

የእንሰት በሽታ በዘላቂነት ለመፍታት እንደ ሀገር በምርምር የተረጋገጠ ውጤት ባለመገኘቱ በሽታው ለመቋቋም ከዚህ በፊት አርሶ አደሩ ያለውን ልምድ ይበልጥ በመጠቀም መከላከል እንዳለበት አንስተው ከዚህም ባለፈ የምርምር ተቋማት በሽታ ሊቋቋሙ የሚችሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ እንዲሰሩም አመላክተዋል።

የጉመር ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደገሙ አለሙ የመድረኩ አላማ በወረዳው የመሬት መሸርሸርና ናዳ አደጋ ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከእንሰትና ከሰብል ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የምርምር ማዕከላት ለችግሩ በቂ ምርምር እንዲያካሂዱ ያነሱት አቶ ደገሙ ከዚህም ባለፈ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የመካናይዜሽንና የእንሰት መፋቂያ ቴክኖሎጂ ለማቅረብ መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

በወረዳው በእንሰሳት ዘርፍ ውጤታማ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝና በተለይም በዝርያያ ማሻሻልና በተደራጁ ወጣቶች የአሳ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እየተመረተ ያለው ምርት ወደ ገበያ ለማውጣት የገበያያ ትስስር ለመፍጠር ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የምርምር ማዕከላት የወረዳው አርሶ አደር ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን በዘላቂነት በመፍታት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት በወረዳው በኤጂፒ ፕሮግራም በግብርና ዘርፍ የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲሳለጥ፣ የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን፣ የአርሶ አደሩና የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች አርሶ አደሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተው እያደረገው ያለው ተግባር በቀጣይም አጠናክሮ ማስቀጠል ይኖርበታል።

የማህበረሰቡ የምግብ ዋስትና የሆነው እንሰት ላይ የተለያዩ ምርምር በማካሄድ የእንሰት በሽታ ለመፍታት የምርምር ማዕከላት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ጠይቀው ከዚህም ባለፈ የወረዳው የመሬት አሲዳማነት በዘላቂነት ለመፍታት የኖራ አቅርቦት በተገቢው እንዲቀርብላቸውም ጠይቀዋል።

በወረዳው የመሬት መሸርሸርና ናዳ መኖር፣ የግብአት አቅርቦት የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ፣ በእንሰሳት ዘርፍ የዘርና የፈሳሽ ናይትሮጅን እጥረትና ሌሎችም በዘርፉ ያሉ ችግሮችን እንዲቀረፍላቸው አንስተዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *