የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የሚሊሻ አባላት ለማጠናከር በሚሰራው ስራ ሁሉም የበኩሉን ማገዝ እንዳለበት የጉራጌ ዞን ሚሊሻ ጽህፈት ገለጸ።

መምሪያው የ2016 በጀት አመት የመጀመሪያ ግማሽ አመት እቅድ አፈጻጸምና የቀጣይ ወራት እቅድ ላይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ሚሊሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ገብሬ በግማሽ በጀት አመቱ የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚሊሻ አባላት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በዚህም የሚሊሻ አባላት የመመልመልና የማደራጀት፣ የማሰልጠንና ለማሰማራት በተሰራው ስራ ጠንካራ የሚሊሻ አባላት ማፍራት ተችሏል።

ከዚህም ባለፈ የሚሊሻ አካላት የደንብ ልብስ የማልበስና ትጥቅ የማሟላት ስራ መሰራቱን የጠቀሱት አቶ ደሳለኝ ትጥቅ ያላቸውን የሚሊሻ አባላት በተገቢው እንዲይዙና ለሰላም ስራ እንዲጠቀሙበት በተፈጠረው ግንዛቤ የተሻለ ለውጥ መጥቷልም ብለዋል።

ማህበረሰቡን ያለምንም ስጋት የእለት ተእለት ስራቸውን እንዲያከናውኑና በክብረ በዓላት ወቅት የማህበረሰቡና የአካባቢው ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱንም አመላክተዋል።

ለማህበረሰቡ በተፈጠረው ግንዛቤ ማህበረሰቡ ለሚሊሻ አባላት የደንብ ልብስ የማልበስ ስራ፣ ህገወጥ ኮንትሮባንድና ህገወጥ የህጻናት ዝውውር ፣ ስርቆቶች፣ ገቢ ለማስመለጥ ብሎም ሌሎችም ህገወጥ ስራዎች ሲሰሩ የነበሩ አካላትና ተጠርጣሪዎችን ከሚሊሻ ጎን በመቆም ጥቆማ በመስጠት ለህግ የማቅረብ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።

የአካባቢው ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከሰላምና ጸጥታ፣ ከፖሊስ፣ ከአስተዳደር ጋር በመቀናጀት በተሰራው ስራ የተሻለ ለውጦች መመዝገባቸውንም አስረድተዋል።

በቀጣይም ሚሊሻ በመመልመልና በማሰልጠን የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ሊያስጠብቅ የሚችል ሚሊሻ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ሁሉም ሊያግዝ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዞኑ ህገወጥነቶች፣ ሌብነቶችና ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች እንዳይፈጠሩ መረጃ በማሰባሰብ የስጋት አካባቢዎችን በመለየት ከስጋት እንዲቀንስ እንደሚሰራም አመላክተዋል።

በተለያየ ምክንያት የተጓደሉ የሚሊሻ አባላት የሟማላትና ለሚሊሻ አባላት የአመለካከትና የክህሎት ክፍተት ለመሙላት ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመው የሚሊሻ የደንብ ልብስ ለማሟላት መንግስትና ህብረተሰቡ እንዲያግዙም ጠይቀዋል።

በቀጣይ ህብረተሰቡ ህገወጦችን በመጠቆም፣ ተጠርጣሪዎችን ለይቶ ለህግ በማቅረብና በማደን፣ ሊፈጠሩ የሚችሉ ስጋቶችን በመቀነስ፣ የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋዎች እንዲቀንሱ ከሚሊሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት የማህበረሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ላይ በትኩረት መስራት ይኖርብናል።

ህብረተሰቡን በማስተባበርና በመንግስት ለሚሊሻ አካላት የደንብ ልብስ ማሟላት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለሚሊሻ አባላት የእቅም ማጎልበቻ ስልጠና ከመስጠት ባለፈ ማጠናከር እንደሚገና ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *