የሀገራዊ የምክክር መድረኩ የታለመለት ሃገራዊ ዓላማ እንዲያሳካ መላዉ ህብረተሰቡና በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

በጉራጌ ዞን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ የሚሰጡ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች ለመምረጥ የሚያስችለው የውይይት መድረክ ዛሬም በወልቂጤ ከተማ ቀጥሎ ውሏል።

የሀገራዊ የምክክር መድረኩ የታለመለት ሃገራዊ ዓላማ እንዲያሳካ ህብረተሰቡና በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሀላፊነት ሊወጡ ይገባል።

የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ እንዳሉት በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ ለችግር የዳረጉትን ምክንያቶች በመለየትና ተገቢውን ምክክር በማድረግ ምክረሃሳቦችን በማሰባሰብና መፍትሄ በመስጠት ይፈታሉ ብለዋል።

እስካሁንም በተባባሪ አካላት ድጋፍ ከተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከሚገኙት የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሰጡትን አጀንዳዎች በማሰባሰብ ለኮሚሽኑ የሚያቀርቡ ተወካዮች መለየት መቻሉንም ነው የተናገሩት።

ይህ መድረክም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሰጡትን አጀንዳዎች በማሰባሰብ ለኮሚሽኑ የሚያቀርቡትን ተወካዮች ከየማህበራዊ መሰረቶቻቸው እንዲመርጡም ምቹ ሁኔታ የሚፈጠርበት ነውም ብለዋል።

በመሆኑም ከማህበረሰቡ ክፍሎች ሁለት ሁለት ተወካዮች ከአንዳንድ ተጠባባቂ ጋር እንደሚመርጡም ተገልጿል።

ሂደቱም ተአማኒነትና ትጋትን የሚጠይቅ እንደሆነም ከግንዛቤ መግባት እንዳለበትም ተናግረው ምርጫው በሚካሄድበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጎ ሃገራዊ ሃላፊነትን የሚሸከሙ አካላት ሊመረጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም መድረኩ እጅግ አስፈላጊና በጉጉት ሲጠብቁት እንደነበር በመግለፅ እንደሃገር ያሉብንን ችግሮች መንስኤዎቻቸው በመለየትና በጋራ በመምከር ሁሉን አቀፍ የሆነ ሃገራዊ መፍትሄ ያመጣል ሲሉም ተናግረዋል።

ሃገራዊ ምክክሩ ሲጠናቀቅ እስከ ዛሬ ሳንግባባቸው በቁዮ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ተፈጥሮ የተሻለችና ለሁሉ እኩል የሆነች ሃገር ትኖረናለች የሚል ተስፋ እንደሰነቁም ነው ተሳታፊዎቹ የገለፁት።

ይህ ትልቅና መሰረታዊ አላማ ያነገበ ኩነት የተሳካ እንዲሆን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በቅንነትና በትጋት ሃገራዊ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል ተሳታፊዎቹ።

ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተወክለው የመጡ ተሳታፊዎች የሚወክሏቸውን አካላት የሚመርጡበትና ለመረጧቸው ሰዎች የአጀንዳ ሃሳብ የሚያካፍሉበት እንደሚሆንም ነው ከመድረኩ መረሃግር ለመረዳት የተቻለው ።

በዛሬ መድረክም የጌቶ፣የጉመር፣የቸሃ፣ወረዳዎች እንዲሁም የአረቅጥ እና የእምድብር ከተማ አስተዳደሮች ተወካዮች እየተሳተፉ እንደሚገኙም ታዉቋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *