የሀገሪቱ ሁለንተናዊ ልማትና ሰላም ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የወጣቶች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ከመንግስት ጎን በመቆም ሊያግዙ እንደሚገባ ተገለጸ።

በጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የወጣቶች ሊግ “እኔ ለሀገሬ የሰላም ዘብ ነኝ” በሚል መሪ ቃል የማጠቃለያ የወጣቶች የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የርዕዮተ ዓለምና አቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሱልጣን አሽሮ በመድረኩ ተገኝተው እንዳሉት የሀገሪቱ ሁሉንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው።

በክልሉ በአንዳንድ አካባቢ የሚፈጠሩ የሰላም ችግሮችን ለመቅረፍ መንግስት ህግ ለማስከበር በሚያደረገው ጥረት ህብረትሰቡና ወጣቱ ማገዝ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የወጣቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ያነሱት ኃላፊው ለዚህም ወጣቱ የስራ ባህሉን በመቀየር ስራ ፈጣሪ በመሆን ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መኖራቸውን አንስተው እነዚህም መንግስት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሰላም ዋጋ ወሳኝ በመሆኑ ወጣቱ ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ክብሩ ፈቀደ በበኩላቸው ሀገሪቷ የጀመረችውን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እውን እንዲሆኑ ወጣቶች ሚናቸውን በተገቢው መወጣት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

እንደ ዞን ወጣቱ ከፓርቲና ከመንግስት ጎን በመቆም ለልማትና ለሰላም ስኬታማነት የበኩላቸውን ከመወጣት ባሻገር በበጎ ፈቃድ ስራዎች በስፋት መሳተፍ ይኖርባቸዋል።

በተለይም አሁን ላይ ያለው የፖለቲካ ስብራት ለመጠገን በብሄር ጽፈኝነትና በሀይማኖት አክራሪነት ሽፋን የሚሰሩ የፖለቲካ ሸፍጦች፣ አፍርሶ መገንባት፣ ደካማ የስራ ባህል፣ የትብብርና የፉክክር ሚዛን ማጣት፣ ስሜታዊነትና ሌሎችም በተገቢው በመረዳት ለሀገራቸው ሰላምና ሁለንተናዊ ለውጥ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሄኖክ አብድልሰመድ እንደ ሀገር የሚታዩ የሰላም እጦቶችን ለማርገብ መንግስት የህብረተሰቡ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ወጣቱ ማገዝ ይኖርበታል።

ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ሀይማኖት ከሀይማኖት ብሔርን ከብሔር የሚያጣሉ አካላትን መቃወም እንደሚገባ ጠቅሰው ወጣቱ ቴክኖሎጂን በተገቢው በመጠቀም የማህበረሰቡን መልካም እሴት ከማስተዋወቅ ባለፈ ለልማትና እድገት ሊጠቀሙበት ይገባል ነው ያሉት።

የወጣቶች የስብዕና ግንባታ ጋር ተያይዞ የወጣቱ ማዕከላትና መዝናኛ ስፍራዎች ለሚፈለገው አላማ እንዲውሉ መምሪያው እንደሚሰራ ገልጸው በዚህም ወጣቱ ሊያግዝ እንደሚገባ አንስተዋል።

በዞኑ ከበጎ ፈቃድ ስራዎች ጋር ተያይዞ የሚሰሩ ሰፋፊ ስራዎች መኖራቸውን ገልጸው በዚህም ወጣቱ የሚያደርገው ተሳትፎ በበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት የወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መኪ ሀሰን የዞኑ ወጣቶች ከለውጡ የተገኘውን ትሩፋቶች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሁሉንተናዊ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቅሰው ወጣቱ ከብሔርና ከሀይማኖት ጽንፈኝነት በመቃወም ከጸረ ሰላም ሀይሎች ራሳቸውን ከመጠበቅ በማህበረሰባቸው ጉዳይ ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ ወጣቶች እንዳሉት ወጣቱ ከስሜታዊነት በመውጣት ለሰላም ዘብ በመቆም በሀገር፣ በክልል ብሎም በዞንና በአካባቢ ሰላምና እድገት ላይ ከመንግስት ጎን በመሆን መስራት ይገባል ብለዋል።

መንግስት ለወጣቱ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የስራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸው ወጣቱም ስራ ጠባቂ ብቻ ሳይሆን ስራ ፈጣሪ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

የጉራጌ ህዝብ ከፓርቲ ለመነጠል የሚደረገው ጥረት ትክክል ያልሆነና ህብረተሰቡና ወጣቱ የማይመጥን እንደሆነ ጠቅሰው የጉራጌ ማህበረሰብ ለሀገራዊ ለውጡ ብዙ ዋጋ መክፈሉን ያነሱት ወጣቶቹ ህብረተሰቡ ከፓርቲው ጎን በመቆም የሚያደርገውን እገዛው በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀልም አመላክተዋል።

አክለውም የክልሉና የዞኑ መንግስት የወልቂጤ ከተማ ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ መሰራት እንዳለባቸው ገልጸው ይህም በሚደረገው ጥረት ወጣቱ እንደሚይግዝ ገልጸዋል።

በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ችግሮች መኖሩን ጠቅሰው ይህም የክልሉና የዞኑ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባና ወጣቱም ማገዝ እንዳለበት ጠቅሰዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *