ዞናዊ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት በወልቂጤ ከተማ በርሆቦት ትምህርት ቤት በይፋ ተጀመረ።


በዞኑ የተጀመረው ክትባት ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ።

ክትባቱ በይፋ ያስጀመሩት የተገኙት የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ እንደገለጹት እንደ ሀገር ከጡት ካንሰር ቀጥሎ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ገዳይ መሆኑንና ይህም አደገኛና ሴቶች በበሽታው የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው።

በዞኑ በዛሬው እለት በወልቂጤ ከተማ ርሆቦት ትምህርት ቤት የተጀመረው ክትባት ከ25 እስከ 29 እንደሚቆይ ጠቅሰው በዚህም እድሜያቸው 14 አመት ለሞላቸው ልጃገረዶች የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም የሚሰጠው ክትባት ውጤታማ እንዲሆን ጤና፣ ትምህርትና ሴቶች ህጻናት ተቋማትና ሌሎችም በመቀናጀት እንዲሰሩም አስገንዝበዋል።

በሽታው ከተከሰተ በኃላ የሚያሳድረው ማህበራዊና ኢኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው እድሜያቸው 14 የሞላቸው ልጃገረዶች እንዲከተቡ ማድረግ ላይ ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

በጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ የእናቶች ህጻናት ጤናና ስርአተ ምግብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቸሩ አስፋው የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ የሚተላለፈው በግብረስጋ ግንኙነት ወቅት በመሆኑ ክትባቱ በካንሰር በሽታ የሚፈጠረው ስቃይና ሞት እንዲቀንስ ለማስቻል እንደሆነ አመላክተዋል።

ክትባቱ ከመጀመሩ በፊት በዞኑ ለሁሉም መዋቅር ጤና ባለሙያዎችና ኤክስቴንሽኖችና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ስልጠና ከመስጠት ባለፈ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አስረድተዋል።

እንደ ዞን 16 ሺህ የሚሆኑ ልጃገረዶች ክትባቱ እንደሚወስዱ ገልጸው ክትባቱ እንዲሳካ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ክትባቱ ምንም አይነት የጎኒዮሽ ጉዳት የሌለው በመሆኑ ሁሉም ልጃገረዶች ያለምንም ፍራቻ የጤና ባለሙያ የሚሰጣቸውን ክትባት መውሰድ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የወልቂጤ ከተማ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ወርቁ በከተማው ከ4ሺህ በላይ ተማሪዎች ክትባቱ እንዲወስዱና በዚህም በዛሬው እለት በከተማው በሁሉም ትምህርት ቤቶች ክትባቱ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

እንደ ሀገር በማህጸን በር ጫፍ ካንሰር የተጠቂዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ተከትሎ በሽታው ለመከላከል እድሜያቸው 14 አመት ለሞላቸው ልጃገረዶች ክትባቱ እንዲወስዱ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *