ዞኑ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ።

በዞኑ የሚገኙ ደረጃ ሀ፣ ለና ሐ ግብር ከፋዮች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ግብር መክፈያ ማዕከል ተገኝተው ግብርና ታክሳቸው እንዲከፍሉ የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ጠየቀ።

መምሪያው የ2016 የግብር ዘመን የንቅናቄ መድረክ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ክብሩ ፈቀደ በመድረኩ ተገኝተው እንዳሉት ፍትሃዊ የግብር አከፋፈል ስርአት እንዲኖር በማድረግ ዞኑ የሚያመነጨውን ገቢ ለመሰብሰብ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል።

በዞኑ ሁሉም መዋቅሮች ወጥነት ያለው ገቢ መሰብሰብ እንዳለባቸው ያነሱት አቶ ክብሩ በቀጣይ ግብርና ታክሳቸው በወቅቱ በማይከፍሉ ነጋዴዎች ላይ አሰራሩ ተከትሎ ተገቢውን ቅጣት መስጠት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ረሻድ እንዳሉት በዞኑ ከ18 ሺህ በላይ የደረጃ ሀ፣ ለና ሐ ግብር ከፋዮች ያሉ ሲሆን ከነዚህም ከ1መቶ 73 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል።

ግብር ከፋዮች ከሀምሌ 1 እስከ ሀምሌ 5 ድረስ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ በግብር መሰብሰቢያ ማዕከላት በመምጣት ግብርና ታክሳቸው አሳውቀው መክፈል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ለዚህም መምሪያው የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አመላክተው ግብር ከፋዮች ላላስፈላጊ ቅጣት እንዳይዳረጉ በመክፈያ ማዕከል ተገኝተው እንዲከፍሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ስራው ውጤታማ እንዲሆን የተጀመረው የግንዛቤና የአመለካከት ስራዎችን በማጠናከር በተደራጀ መልኩ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚሰራ ያነሱት አቶ ሙራድ ከዚህም ባለፈ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በዞኑ ግብርና ታክሳቸው በወቅቱ አሳውቀው የሚከፍሉ ግምባር ቀደም ግብር ከፋዮች በመኖራቸው አመስግነው ለነዚህም የማበረታቻና እውቅና የመስጠት ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት ዞኑ የሚያመነጨውን ገቢ በተገቢው ለመሰብሰብ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አንስተዋል።

የታቀደው እቅድ ውጤታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት እገዛቸው ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *