ዋርካ ኢትዮጵያ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጠቅላላ ሆስፒታል ጋር በጋራ በመሆን ለ5 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ነፃ የአይን ሞራ ቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና ግብረ ሰናይ ድርጅቱ በነፃ የአይን ሞራ ቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው  ተጠቃሚ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች  ታላቅ ደስታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። 

የዋርካ ኢትዮጵያ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ሀገር በቀል ተራድኦ ድርጅት አስተባባሪ አቶ ኢሳያስ ናስር እንደገለጹት ድርጅቱ በ2013 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ከውጭ የUS ሙስሊሜኤድ ተራድኦ ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን በጉራጌ ዞን ማህበሰብ ውስጥ በጤና ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ድርጅቱም የአይን ሞራ ቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የገለፁት አስተባባሪው በዚህም በዞኑ ካሉ መዋቅሮች ጥናት ተደርጎ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ ጌታና ገደባኖ ጉታዠር ወለኒ ወረዳና በተጨማሪም ለወልቂጤና ለአከባቢው ማህበረሰብ አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑንም አብራርተዋል። 

አክለውም ህክምናው በመጀመሪያ ዙር 150 የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ ኢሳያስ በቀጣይም ለ1000 የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ ነው ብለዋል።

ይህ በብር ሲተመን ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ወጪ አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

አያይዘውም በቀጣይ ሁሉም ለዞኑ መዋቅሮች አገልግሎቱ ለመስጠት መታቀዱንም ተናግረዋል።

እንደ አቶ ኢሳያስ ገለፃ ነፃ ህክምናው በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ለመታከም አቅም ለሌላቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚሰጥ መሆኑንና በዚህም ሙሉ ወጪያቸውን በመሸፈን ያለባቸውን የማየት ችግር ለመቅረፍ እየሰራ ነው ብለዋል።

ይህ ነፃ የአይን ቀዶ ህክምና አገልግሎት ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላደረጉ ተቋማት ለወልቂጤ ዩንቨርሲቲ፣ ለጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ፣ ለወልቂጤ ከተማ ጤና ፅ/ቤትና በአገልግሎቱ ተሳትፎ ላደረጉ ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር አብድራሂም በድሩ በበኩላቸው ወልቂጤ ዩንቨርስቲ የህብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ ከዋርካ ሀገር በቀል ተራድኦ ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ለተከታታይ 5 ቀናት የሚቆይ ዘመቻ ለ150 የሞራ ግርዶሽ ችግር ያለባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎችን ከተቋሙ ስፔሻሊስት ሀኪሞችና ከሌሎች ረዳት ባለሙያዎች ጋር በመሆን አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

ዶ/ር አብድራሂም አክለውም ዋርካ ሀገር በቀል ተራድኦ ድርጅት የህብረተሰቡን ችግር በመረዳት ላደረገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።

የአይን ቀዶ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር ቃል ኪዳን ኮርዲሳ ቀዶ ህክምና ሲያደርጉ አግኝተን እንዳነጋገርናቸው በቲም በመሆን የአይን ሞራ ግርዶሽ ያለባቸው ህብረተሰብ በመለየት ህክምና እየሰጡ መሆኑና አገልግሎት በመስጠታቸውም የህሊና እርካታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

አክለውም የአይን ሞራ ግርዶሽ  በሀገራችን አይነ ስውርነትን የሚያስከል በመሆኑ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከዋርካ ሀገር በቀል ድርጅት ጋር በመተባበር የህብረተሰቡ ችግር በመረዳት ነፃ የአይን ሞራ ህክምና  አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረጉ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

የአይን ሞራ ግርዶሽ ነፃ ቀዶ ህክምና ሲያደርጉ አግኝተን ያነጋገርናቸው ታካሚዎች እንደተናገሩት ከዚህ በፊት ለመታከም አቅም እንዳልነበራቸው ጠቁመው ነፃ አገልግሎት በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።

አክለውም በህክምናው ወቅት ባለሙያዎች በቂ እንክብካቤ እያደረጉላቸው መሆኑን የገለፁት ታካሚዎቹ የህብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ ወልቂጤ ዩንቨርስቲና ዋርካ ግብረ ሰናይ ድርጅት እያደረጉት ያለው ተግባር አመስግነዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡

Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone

Website:- https://gurage.gov.et

Telegram:- https://t.me/comminuca

Youtub: –https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *