በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ በገጠር የስራ እድል ፈጠራ ውጤታማ የሆኑ ወጣቶች የስንዴ ማሳ ተጎበኘ፡፡
የደቡብ ክልል የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢረጋ ብርሃኑ በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ በገጠር የስራ እድል ፈጠራ ውጤታማ የሆኑ ወጣቶች የስንዴ ማሳ በጎበኙበት ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ የሚገኙ ስራ አጥ ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች የሚመረቁ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ተከትሎ የሚፈጠረው የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ ቢሮው በግብርና፣ በአገልግሎትና በአምራች ዘርፍ እንዲደራጁ ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ በገጠር የስራ እድል ፈጠራ ውጤታማ የሆኑ ወጣቶች ያከናወኑት ኩታገጠም የስንዴ ማሳ አበረታችና በአርአያነት የሚጠቀስ ሲሆን የወጣቶቹ ምርጥ ተሞክሮ በመቀመር በክልሉ ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።
ወጣቶች ጊዜያቸው፣ ጉልበታቸውና እውቀታቸውን ተጠቅመው በተለያዩ የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ በማድረግ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት እንዲላቀቁ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አቶ ቢረጋ ገልጸዋል ።
የጉራጌ ዞን የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ አመርጋ በበኩላቸው በሩብ አመቱ 6ሺህ 317 በከተማና በገጠር የሚኖሩ ስራ አጥ ወጣቶች ስራ ለመፍጠር ታቅዶ 5 ሺህ 803 ወጣቶች በጊዜያዊና በቋሚ የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ አፈጻጸሙም 91 በመቶ መሆኑን በመግለፅ።
በገጠር የሚገኙ ስራ አጥ ወጣቶች የወል መሬት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይሰራል ያሉት አቶ አበበ ወጣቶች የሚፈጠርላቸው ግንዛቤ ተጠቅመው ውጤታማ በሚያደርጋቸው የግብርና ስራዎች መሰማራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
ለዚህ ማሳያ በሶዶ ወረዳ የጀርሳ ሌሌ ቀበሌ ወጣቶች በ28 ማህበራት የተደራጁ140 ወጣቶች በኩታ ገጠም ያመረቱት የስንዴ ማሳ ከራሳቸው አልፎ ለሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት አጋዥ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም ወጣቶች የሚጠይቋቸው የኮምባይነር፣ የመስኖ ልማት ግብዐት ለማጠናከር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡
ወጣት ሞገስ ጨመረ እና ወጣት ኤርሚያስ ዳንኤል በገጠር የስራ እድል ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ ወጣቶቹ ገለጻ ጽህፈት ቤቱ በገጠር ስራ እድል ፈጠራ ጠቀሜታ እና ውጤታማነት ላይ ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል ።
ወጣቶቹ ከግንዛቤ ባለፈ የወል መሬትና ምርትንና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎች እንዲቀርብላቸው በመደረጉ ተጠቃሚ እንደሆኑ አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ ምርትን ከተሰበሰበ በኋላ ወደ ተጠቃሚው ማህበረሰብ ለማድረስ የመንገድ ልማት ችግር እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል።
አያይዘውም ወጣቶቹ ምርት ሳይባክን አጭዶ ለመወቃት የሚግዝ የኮምባይነር፣ የመስኖ ውሃ እና የገበያ ትስስር ጥያቄያቸው መንግስት እንዲመልስላቸው ጠይቀዋል።
በዚህም ያላቸውን እውቀት፣ ገንዘብና ጉልበታቸውን በመጠቀም በዘርፉ የሚፈልገውን ምርት ለማምረት አቅም እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx