ወጣት ተስፋ ንዳ ከማህበራዊ ሚዲያ ቤተሰቦቹ የ100 ብር ቻሌንጅ ገንዘብ በማሰባሰብ የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም የዞንና የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ተካሄደ።

የጉራጌ ዞን የአስተዳደር ተወካይ አቶ ሚነወር ሀያቱ በፕሮግራሙ ተገኝተው እንዳሉት ወጣት ተስፋ ንዳ በማዕከሉ ለአረጋውያን ማዕድ ከማጋራቱም ባለፈ የአልባሳትና የፉርኖ ዱቄት ድጋፍ በማድረጉ አመስግነዋል።

ወጣቱ ማህበራዊ ሚዲያ ለበጎ አላማ በማዋል ከማህበራዊ ሚዲያ ቤተሰቦቹ ገንዘብ በማሰባሰብ በወልቂጤ ከተማ አረጋውያን በመመገብ ያደረገው መልካም ተግባር ሁሉም ማስቀጠል እንዳለበት አስረድተዋል።

በዞኑ ቤተ እምነቶች ከእምነት ስራቸው ባሻገር በማህበራዊ ስራ በርካታ ተግባራት እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀው በቀጣይም አቅም ደካሞችን ይበልጥ መደገፍ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የጉራጌ ማህበረሰብ የቆየ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት ያለው በመሆኑ ይህንን እሴቱ ይበልጥ በመጠቀም በዞኑ ያሉ አቅም ደካሞችን ለመደገፍ ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ንቅበሽዋ በበኩላቸው አቅም ደካሞች መርዳት የህሊና እርካታ ከማግኘት ባለፈ እምነትም ጭምር የሚያዝ በመሆኑ ተግባሩ ሊጠናከር ይገባል።

በዛሬው እለት ተስፋ ንዳ ከማህበራዊ ሚዲያ ቤተሰቦቹ ገንዘብ በማሰባሰብ በወልቂጤ ከተማ ለአረጋውያን ያደረጉት የማዕድ ማጋራት አርአያነት ያለው ተግባር በመሆኑ በከተማው ያሉ አቅመ ደካማ ወገኖች ሁሉም አቅሙን በሚችለው መደገፍ እንዳለበት ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በከተማው ያሉ አቅመ ደካማ ወገኖች በበዓላትና በሌሎችም ወቅት ማዕድ የማጋራትና የመደገፍ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ይህ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በእምድብር ሀገረ ስብከት የወልቂጤ ቅዱስ ሚካኤል ቁምስና አገልጋይ አባ አማረ ገብሬ ተስፋ ንዳ በማዕኩሉ ለአረጋውያን ያደረገው በጎ ተግባር ሁሉም ሊያስቀጥለው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ደራሲና የማስታወቂያ ባለሙያ ወጣት ተስፋ ንዳ በበኩላቸው ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ አላማ በማዋል በማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች በ100 ብር ቻሌንጅ ገንዘብ በማሰባሰብ ለ150 አረጋውያን በወልቂጤ ከተማ የማዕድ ማጋራትና የአልባሳት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ለስድስት ተከታታይ ጊዜያት በማህበራዊ ሚዲያ ቻሌንጅ ገንዘብ በማሰባሰብ ለበርካታ ወገኖች የስራ እድል መፍጠራቸውና ማዕድ ማጋራታቸውን አስታውሰው በዛሬው እለትም በወልቂጤ ከተማ የቅዱስ ሚካኤል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአረጋውያን የምገባ ማዕከል የማህበራዊ ሚዲያ ቤተሰቦቹ እምነት፣ ብሔር ሳይገድባቸው የሚችሉት መዋጮ በማድረግ ለአረጋውያን ተግባሩ ማስቀጠሉን ገልጸዋል።

በዞኑ አረጋውያንን በዘላቂነት ለመደገፍ የአረጋውያን መርጃ ድርጅት ሊከፈት ይገባል ያሉት ወጣት ተስፋ ለዚህም የእምነት ተቋማት፣ መንግስት፣ ባለሀብቶችና ሌሎችም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በቀጣይም መሰል ስራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያነሱት አቶ ተስፋ የማዕከሉ አረጋውያን ለመርዳት ሁሉም በሚችለው አቅም ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል ብለዋል።

በዞኑ በርካታ ድጋፍ የሚሹ አቅመ ደካማ ወገኖች መኖራቸውን ገልጸው በማህበረሰቡ መንገድ ላይ ወጥቶ መለመን እንደ ከባድ ነውር መቆጠሩን ተከትሎ በርካታ አቅመ ደካማ ወገኖች በተለያየ ቦታ ችግር ውስጥ በመሆናቸው ሁሉም ይህንን ተረድቶ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል ብለዋል።

በወልቂጤ ከተማ የቅዱስ ሚካኤል ካቶሊካዊት አረጋውያን የምገባ ማዕከል የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ደረጄ እስጢፋኖስ በማዕከሉ 150 አረጋውያን መኖራቸውን ገልጸው በዛሬው እለት አመራሮች በተገኙበት ማዕድ የማጋራት ስራ ተሰርቷል።

በማዕከሉ ያሉ አረጋውያንን ለመርዳት ተስፋ ንዳ በሰራው መልካም ስራ ተደስተው ይህ ድጋፍ ሁሉም ማስቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።

በማዕድ ማጋራት ፕሮግራም ያገኘናቸው አረጋውያን እንዳሉት አቶ ተስፋ ንዳ ችግራቸውን በመረዳት ማዕድ ከማጋራት ባለፈ ባደረገላቸው የአልባሳት ድጋፍ እጅግ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ለተደረገላቸው ድጋፍም ለአቶ ተስፋና የማህበራዊ ሚዲያ ቤተሰቦቹ አመስግነው መሰል ድጋፎች በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *