ክስፖርት የሚሆኑ የጥራጥሬና የቅባት ሰብሎች ጥራትና ቁጥጥር ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮ በምርት ጥራትና ቁጥጥር ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ከባለ ድርሻ አላት ጋር በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው በመድረኩ ላይ እንዳሉት ክልሉ ያለውን አቅም በመለየት ለኤክስፖርት የሚሆኑ የጥራጥሬና የቅባት ሰብሎች ጥራትና ቁጥጥር ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ እየሰራ ነው።

በዚህም ከእህል ሰብሎች ሰሊጥ፣ ቦሎቄና ዥንጉርጉር ቦሎቄ ከ20 ሜትሪክ ቶን በላይ ኤክስፖርት በማድረግ 14 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል።

ሆኖም ክልሉ ካለው የጥራጥሬና የቅባት ሰብሎች የማምረት አቅም አንጻር የኤክስፖርት መጠን በሚፈለገው የጥራት ደረጃ እያደገ ባለመሆኑ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ኃላፊው ተናግረዋል።

በክልሉ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማዕከል ባለመኖሩ የሚመረቱ የኤክስፖርት ምርቶች ወደ ሌሎች አካባቢዎች በሚጓጓዙበት ወቅት ለኮንትሮባንድ ንግድ ተገላጭ በመሆናቸው ህገ ወጥ የግብይት ስርዓቱን በመቆጣጠር ወደ ህጋዊነት ለማምጣት በትኩረት እንደሚሰራ አቶ ዳንኤል ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ብርሃኔ በበኩላቸው ክልሉ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቀነስ የሚያስችሉ የኤክስፖርት ምርቶች ለይቶ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች በመቅረፍ የምርት ጥራትና መጠን ለማሳደግ አበረታች ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ በርካታ የኤክስፖርት ምርት አምራቾችና ላኪዎች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ መላኩ ጥራት ያለው ቀይ ቦለቄ በከፍተኛ ደረጃ የሚመረት ሲሆን በኮንትራት ፋርም ሰሊጥ ማምረት መጀመሩን ተናግረዋል።

ለኤክስፖርት የሚሆን 5 ሺህ 95 ቶን በሎቄና 12 ቶን ሰሊጥ መሸኘት እንደተቻለንና በቀጣይ ከዚህ የበለጠ ምርት በጥራትና በመጠን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው እንደሚሰሩ አብራርተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በክልሉ የምርት ገበያ ማዕከል ባለመኖሩ ምርት በማጓጓዝና በመጋዘን በማራገፍ ሂደት የሚደርስባቸውን እንግልት እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል።

ህገ ወጥ ደላሎች የተሳሳተ መረጃ በመስጠት የንግድ ስርዓቱ የሚያዛቡ በመሆናቸው መንግስት ጥብቅ እርምጃ ሊወስድባቸው እንደሚገባና በክልሉ የምርት ገበያ ማዕከል እንዲገፈትላቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በመድረኩ የቢሮው የስራ ኃላፊዎች፣ የዞንና ልዩ ወረዳ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያና ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ ኤክስፖርተሮች እንዲሁም ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *