ክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህል ቱሪዝም ከጉራጌና ከምስራቅ ጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያዎች ጋር በመሆን Lela trail በጉራጌና በምስራቅ ጉራጌ ዞኖች የሚገነቡ የእንግዳ ማረፊያ(guest house) ግንባታ የውል ስምምነት ተፈራርመዋል።

በፊርማ ስነ ስርአቱ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትልና የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኑሪ ከድር እንዳሉት በክልሉ በርካታ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሮአዊ እምቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች መኖሩን ጠቁመው በክልሉ ከነዚህም ውስጥ የጉራጌ ዞን አንዱ ነው።

በዞኖቹ Lela tours የእንግዳ ማረፊያ ለመገንባት የሚያስችል ጥያቄ ለቱሪዝም ሚኒስተርና ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በደብዳቤ በመጠየቅ በዞኖቹ ያሉትን መልከአምድር በመጠቀም የማህበረሰብ ቱሪዝም/community tourism ስራ ለመስራት የሚያስችለውን የግብ ስምምነት መፈራረማቸውን ተናግረዋል።

አክለውም በዞኖቹ ማህበረሰቡ ያካበታቸው ሰፋፊ ሀብቶች መኖራቸውና ለቱሪዝም ዘርፉ ምቹ መሆናቸውን ያነሱት ኃላፊው ፕሮጀክቶቹ ለማህበረሰቡ የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የተለያዩ አገልግሎቶች እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ በመሆን ውጤታማ እንዲሆኑና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህል ቱሪዝም ቢሮ እገዛው አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ በበኩላቸው ጉራጌ ዞን እምቅ ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እንዲሁም ሀይማኖታዊ የቱሪዝም መዳረሻዎች ያለው በመሆኑ ካለው እምቅ የቱሪዝም ጸጋዎችን ከመጠቀም አንጻር ገና በርካታ ስራ እንደሚጠይቅ አመላክተዋል።

በዞኑ የመስቀልና የአረፋ በዓል ተከትሎ በርካታ ቱሪስቶች ወደ ዞኑ በመምጣት ጉብኝት እንደሚያደርጉ ጠቁመው ይህም የማህበረሰቡ እንግዳ ተቀባይነት፣ ምቹ የአየር ጸባይ፣ ምንም አይነት የደህንነት ስጋት የሌለበት መሆኑ ቱሪስቶች በስፋት ወደ ዞኑ በመምጣት እንደሚጎበኙም ጠቁመዋል።

ይህንን የተረዳው lela trail ‘Rural development tourism community’ የሚል ፕሮጀክት በመቅረጽ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የቱሪስቶች የእንግዳ ማረፊያ ለመገንባት በምሁር አክሊል ወረዳ በአንዝሬና ኤቸነ ቀበሌ ዋዠራ ጥብቅ መንደር እንዲሁም በምስራቅ ጉራጌ ዞን የማህበረሰቡን ባህል በሚገልጽ መልኩ እንደሚገነባ ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቶቹ መገንባት ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የማህበረሰቡን እሴቶችን ለአለም ህዝብ በማስተዋወቅ የገቢ ምንጭ ለማግኘት ሚናው የላቀ ነው።

የLela trail አስተባባሪ አቶ ማርኮ ደጋስፐር እንደገለጹት ዞኖቹ ለቱሪዝም ዘርፉ ምቹ ከመሆናቸውም ባሻገር የማህበረሰቡን የአኗናር፣ የአመጋገብና ሌሎችም እሴቶቹ ተመራጭ በመሆኑ በሁለቱ ዞኖች ፕሮጀክቱ እንደሚገነቡ እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።

የፕሮጀክቶቹ ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ሲሳይ ማህበረሰብ ያማከለ ቱሪዝም መገንባት ማህበረሰቡ ተጠቃሚ ከማረጋገጥ ባለፈ የቱሪዝም ስራ በባለቤትነት እንዲመራና ባህልና ሌሎችም እሴቶችን ለአለም ህዝቦች የሚያስተዋውቅበት ነው።

በፕሮጀክቶቹ የጉራጌ እሴት በጠበቀ መልኩ በሶስት ቦታዎች የእንግዳ ማረፊያ እንደሚገነቡ ገልጸው ለዚህም ከ170 ሺህ ዶላር በላይ ወጪ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ወደ ስራ ለማስገባት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *