ከ48 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በበጋ መስኖ ስንዴና በመደበኛ መስኖ መልማቱ የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ አዘጅነት ለ2 ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የነበረው ዞን አቀፍ የበጋ የመስኖ ስንዴና መደበኛ የመስኖ ልማት ስራ የመስክ ጉብኝት በማረቆ፣ በምስራቅ መስቃንና በደቡብ ሶዶ ወረዳዎች በማካሄድ ተጠናቋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ እንደገለፁት የመስክ ጉብኝቱ በ2014 የምርት ዘመን አዲስ የሆነውን የበጋ መስኖ ስንዴን በሁሉም ወረዳዎች ያለበትን ደረጃ በማየት አርሶ አደሩ ለማበረታታትና የጎደለውን ለማሻሻል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

1 ሺህ 2 መቶ ሶስት ሔክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴና 47 ሺህ 5 መቶ 57 ሄክታር መሬት በመደበኛ መስኖ በጥቅሉ ከ48 ሺህ 760 ሄክታር መሬት በጉራጌ ዞን ባሉ ወረዳዎች መልማት መቻሉን ተናግረዋል።

አጠቃላይ ከለማው መሬት ከ40 ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴ እና በመደበኛ መስኖ 9 ነጥብ 75 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

በመስኖ ስራ ዞኑ ከአመት አመት የተሻለ አፈፃፀም ማሳየቱን ተናግረዉ በመስኖ ልማት የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን ወደ ሁሉም ወረዳዎችና አርሶ አደሮች ለማስፋት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በቀጣይ የምርት ሽፋንን ለማሳደግ በዘንድሮው የታዩትን ጉድለቶች በማረም በተዋረድ መሰራት አለበት የሚሉት አቶ አበራ በሀገር ደረጃ ትርጉም ያለው ተግባር ላይ ተሳትፎ ከማድረግ ባሻገር እንደዞን የግብርና ልማት ስራዎች ውጤታማ እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል።

የአርሶ አደሩን የገበያ ትስስር በተመለከተ በደላሎች ከሚሆን በህብረት ስራ ማህበራትና በዩኒየኖች መሆን እንዳለበት አቶ አበራ አክለው ገልፀዋል።

የጉራጌ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል በጉብኝቱ ላይ እንደተናገሩት በዞኑ ባሉ ወረዳዎች የበጋ መስኖ ስንዴን ማምረት እንደሀገር የሚስተዋለው ያልተረጋጋ ኢኮኖሚ ማረጋጋት ላይ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ሀገራችን በስንዴ እርዳታ አትኖርም የሚለውን የመንግስት መርህ ተግባራዊ ለማድረግ በዚህ ፈታኝ ወቅትና ቦታ በበጋ መስኖ ለማልማት ርብርብ እያደረጉ ላሉ ወጣቶች፣ አርሶ አደሮች፣ እናቶች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመስክ ጉብኝቱ በማረቆ ወረዳ በጎቶ መንዲፋ ቀበሌ የለማ የበጋ ስንዴ እያለሙ ያገኘናቸው አርሶ አደር ለራጉ ኡላ እና አማዶ ደነቦ እንደገለፁት ከዚህ በፊት ከነበረው ግጭት ወደ ሰላም ተሸጋግረው የበጋ መስኖ ስንዴ እና መደበኛ መስኖ ልማት ላይ በመሰማራታቸው ተደስተዋል።

በምስራቅ መስቃን ወረዳ በባቲ ሌጃኖ ቀበሌ ያነጋገርናቸው አርሶ አደር መለሰ ኡርጋቶ እንዳሉት በግጭቱ ምክንያት ያላመረቱበት ወቅት እንደነበር ገልፀው አሁን ሰላም በመስፈኑ ወደ ልማት መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

በደቡብ ሶዶ ወረዳ የኬላ ዙሪያ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አምሳሉ ታደለ እንደገለፁት የበጋ የመስኖ ስንዴና መደበኛ የመስኖ ልማት ላይ ሲያለሙ የመንግስት እገዛ እንዳልተለያቸው ተናግረዋል።

እንደአርሶ አደሮቹ የገበያ ትስስር መንግስት እንዲፈጥርላቸውና ደረጃቸው ከፍ ያሉ ጀነሬተሮች መንግስት ማቅረብ ቢችል በስፋት ለማልማት ዝግጁ መሆናቸው ተናግረዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

በመረጃ ምንጭነት ገጻችን ምርጫዎ ስላደረጉ እናመሰግናለን!!

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:-
https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *