ከ34 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባው የቀቤና ብሔረሰብ የባህል ማዕከል በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተመረቀ።


የቀቤና ብሔረሰብ ታሪክ፣ ቋንቋና ባህል ጠብቆ ለማቆየት ፣ ለማስተዋወቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ የባህል ማዕከሉ መገንባት ፍይዳው የጎላ መሆኑን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክርቤት ዋና አፈጉባኤ ክብርት ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ ገለጹ።

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ክብርት ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ በምረቃ ስነ ስርአቱ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የቀቤና ብሔረሰብ ባህልን፣ ቋንቋና ታሪክን ጠብቆ በማቆየትና በማሳደግ ረገድ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የባህል ማዕከሉ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

ባህል የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚያከናውኑት የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ስነ ምግባር የቋንቋ፣ የታሪክ፣ የምግብ አዘገጃጀት፣ የአልባሳትና ሌሎችም እሴቶች የባህል አካል ናቸው ብለዋል።
እነዚህን ጠብቆ ለማቆየት ፣ ለማስተዋወቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ የቀቤና ብሔረሰብ የባህል ማዕከል መገንባት ፍይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ በዚህ ዘርፍ ለሚመራመሩ ተመራማሪዎችና ጸሀፊዎች ቋሚ የመረጃ ማዕከል ከመሆንና የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን አስተዋጽኦው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት የተገነባው የቀቤና የባህል ማዕከል ለዞኑ ብቻ ሳይሆን በክልል ደረጃ ሞዴል የሆነ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሁም ለከተማው ተጨማሪ ውበት የሚሰጥ በመሆኑ በህብረተሰብ ተሳትፎ ተአምር መስራት እንደሚቻል ማሳያ ነው።

ባህል የአንድን ህዝብ ማንነት መገለጫ በመሆኑ ባህል ማዕከሉ ለዚህ ደረጃ እንዲበቃ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት አመስግነው በቀጣይም የጥናትና ምርምር፣ የኮንፈረንስ ማዕከል እንዲሆን በማስዋብ የመዝናኛ ማዕከልም እንዲሆን ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የቀቤና ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ ዘይኑ ሻቡዲን የባህል ማዕከሉ ገንብቶ ለማጠናቀቅ በርካታ አመታት ያስቆጠረ ቢሆንም እንኳ በህብረተሰቡ ተሳትፎ መሰል ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ማሳያ ነው።

የባህል ማዕከሉ የብሔረሰቡ ታሪክ፣ ቅርሶችን ማደራጃ፣ የቀቤኒሳ ቋንቋ ማበልጸግያ፣ በቋንቋ ዙሪያ ጥናትና ምርምር የሚደረግበት ማዕከል ጨምሮ የኦጎት አባቶች መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ መስጂድና ሀገራዊ፣ ክልላዊና ዞናዊ ስብሰባዎችን ማስተናገድ የሚችል አዳራሽ ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀቤና ብሔረሰብ ለመልማት ያለው ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡን በማስተባበር በመንገድ፣ በትምህርት፣ በጤናና በውሃ ሰፋፊ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው በቀጣይ በባህል ማዕከሉ ያልተሟሉ ቁሳቁሶች ለሟሟላት ሁሉም እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የቀቤና ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ከማል ሱልጣን በበኩላቸው የቀቤና የልማት ማህበር በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ያሉ የብሔረሰቡ ተወላጆችን በማስተባበርና ከመንግስትና ከሌሎችም የልማት ደጋፊዎች ጋር በጋራ በመሆን የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በዚህም የቀቤና ብሔረሰብ ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋና ሌሎችም እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየትና ለትውልድ ለማሸጋገር በማሰብ የባህል ማዕከሉ በመገንባት ማስመረቅ ችሏል ብለዋል።

ልማት ማህበሩ በቀጣይ የህብረተሰቡን ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክና ሌሎችም እሴቶችን ከማሳደግ በተጨማሪ መንግስት ተደራሽ ባልሆነባቸው የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የልማት ማህበሩ ተገንብቶ ለዚህ ደረጃ እንዲበቃ እገዛ ላደረጉ አካላት አመስግነዋል።

ወይዘሮ ፈቲያ ሱልጣን፣ ሀጅ አባድር ሀጅ አክመልና አቶ አቶ ካፉ አረቦ የበአሉ ተሳታፊ ሲሆኑ በጋራ በሰጡት አስተያየት የባህል ማዕከሉ ተገንብቶ ለምረቃ በመብቃቱ ደስተኛ መሆናቸውን የብሔረሰቡ ተወላጆች ተናግረዋል።

የባህል ማዕከሉ መገንባት የብሔረሰቡን ታሪክ፣ ቋንቋንና ባህል ለማሳደግና ለትውልድ ለቀጣይ ማስተላለፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተሳታፊዎቹ ተናግረው በህብረተሰቡ ተሳትፎ መገንባቱን ጠቁመዋል።

በቀጣይም በባህል ማዕከሉ ያሳየውን ተሳትፎ በሌሎችም የልማት ዘርፎች ላይ አጠናክሮ ማስቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
በእለቱም በበዓሉ ለተሳተፉ የክብር እንግዶችና በባህል ማዕከሉ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ተቋማት ወረዳው የሰርተፍኬት፣ የዋንጫና ሌሎችም ስጦታዎችን አበርክቶላቸዋል።

እንዲሁም ከደቡብ ክልል፣ ከኦሮሚያ፣ ከሲዳማ፣ ፣ ከተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች እንዲህም ልዩ ወረዳ የሰንጋ፣ የብርና የተለያዩ ስጦታዎችን ለቀቤና ወረዳው አበርክተዋል።

በነገው እለትም 3ኛው የቀቤና ብሄረሰብ የታሪክ፤ የባህልና የቋንቋ ሲምፖዚየም እንደሚካሄድም ተገልጿል። በዕለቱም በብሄረሰቡ ምሁራን የተዘጋጁ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *