ከወልቂጤ እና አካባቢዋ ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት የተሰጠ መግላጫ

የወልቂጤ ከተማና አካባቢዋ ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት የአካባቢው ሰላም እና የሕዝቡ ደህንነት ለመጠበቅ በየደረጃው ከሚገኙ የጸጥታመዋቅር አመራር እና አባላት፣ ከየ መዋቅሪ አመራር እና ከሰላም ወዳድ ሕዝባችን ጋር በመቀናጀት በተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ።

ይህንን አንጻራዊ ሰላም ሳይደፈርስ ይበልጥ በማጠናከር በአካባቢው ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን እየሰራ እንደሚገኝ ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስቱ በላከው መግለጫ አመላክቷል።

በመሆኑም በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተጀመረው ስራ ውጤታማ ለማድረግ ህግ የማስከበር ስራ መሰራት እንደሚገባ ተመላክቷል።

ስለሆነም ተጨማሪ ህግ የማስከበር ስራዎችን ለመስራት ያመች ዘንድ ከዛሬ ግንቦት 22/2016 ጀምሮ በተለዋጭ መግለጫ እስከሚሻር ድረስ የሚከተሉትን የሰዓት ገደብ እና ክልከላ ተደርገዋል፦

1) የባለ ሁለት እግር ሞተርነና ባለ ሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች ከምሽቱ 3:00-ንጋት 11:00 ማንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው።

2)ሁሉም መዝናኛ ቤቶች ማለትም ጭፈራ ቤቶች ፣ ክለቦች ግሮሰሪዎች ፣ ፑልና መሰል መሰብሰቢያ ቦታዎች፣መቃሚያ እና ማጨሻዎች ወዘተ ከምሽቱ 4:00 በኋላ አገልግሎት መስጠት እና ያለ በቂ ምክንያት መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው።

3)በየትኛውም ሰዓት በደስታም ሆነ በሃዘን፤ መሳሪያ ፣ርችት መተኮስ እና ማንኛውም አካባቢን የሚያውክ ያልተለመደ ድምጽ ማሰማት በጥብቅ የተከለከለነው።

ከተራ ቁጥር 1 እስከ 3 የተዘረዘሩ ክልከላዎች የተላለፈ ማንኛውም ሰው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድበት ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስቱ ይገልጻል። ስለሆነም የከተማው እና የአካባቢው ነዋሪ የየአካባቢያቸው ሰላም ከመጠበቅ በተጨማሪ በጊዜያዊ ኮማንድ ፖስቱ የተጣሉ ክልከላዎች እንዲያከብር ጥሪ አቅርቧል።

የወልቂጤ እና አካባቢው ጊዜያዊ ኮ/ፖስት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *