ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካሉት 11 ክፍለ ከተሞች በተውጣጡ የባህልና ቱሪዝም አመራሮች ባለሙያዎችና አርቲስቶች። የጥያ አለም አቀፍ መካነ ቅርስ ጎበኙ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝምና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ከፍተኛ የቅርስ ጥናት ባለሙያ የሆኑት መምህር መክብብ ገ/ማሪያም እንደተናገሩት የጉብኝቱ 250 አባላት ያለው የዘርፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ አርቲስቶችና አለም አቀፍ ቅርስ አስመላሽ የዲያስፖራ ምክር ቤት አስተባባሪ ያካተተ መሆኑን ገለጸዋል።

የጉብኝቱ መነሻ ሀሳብ ቁፋሮ የማይፈልጉ እንቁ ሀብቶቻችን አውቀን ለትውልድ ለማሳወቅ እንንዲሁም ዘርፉ ማስገኘት በሚችለው ጥቅም ልክ በመስራት የቱሪዝም እንዱስትሪውን ማሳደግን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል::

ጥንት አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩልን የምንኮራበት የስልጣኔ አሻራ የሆኑ ቅርሶቻችንና ባህሎቻችን ይዘታቸውን ሳይለቁ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ከማድረግ ባሻገር ለጎብኚዎች ቀልብ የሚይዙ የባህል ማዕከላት፣ ደረጃውን የጠበቀ ባህላዊ ምግብ ቤቶች፣ የታሪክ ጥናት ውጤቶች ላይ ሰፊ ሥራ መሰራት እንዳለበት አመላክተዋል።

ሌለው በጠቅላይ ሚንስቴር አብይ አህመድ ዶ/ር ጋባዥነት እንግሊዝ አገር የመጡት የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ የዲያስፖራ ም/ ቤት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አለባቸው ደሳለኝ ቅርሱን ለመጀመሪያ ጊዚ እንዳዩትና እጅግ እንደተደሰቱ ገልጸው ቅርሱ በቂ ጥበቃ እና እንክብካቤ በማድረግ ለትወልድ ተሻጋሪነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል::

አስተባባሪው አክለውም ላለፋት 24 ዓመታት ከኢትዮጵያ የተዘረፉ ቅርሶች በመደራደርና ጥናት በማድረግ በርካታ ቅርሶች እንዲመለሱ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ለአብነት የመቅደላው ጀግና የአጼ ቴውድሮስ ጸጉር እንዲመለስ ከሪቻርድ ፓንክሪያስ ጋር በመሆን አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ጠቅሰዋል።

የዛሬ ስነ-ፈለክ/አስትሮኖሚ/ ያልደረሰበት 9 ዓለማት ባሁኑ ወቅት ወደ 13 እንደደረሱ የሚገልጹት የጥንት አባቶቻችን ግን ገና የህዋ ሳይንስ ያልደረሰባቸው ቀደመው በመድረስ 16ፕላኔቶች እንዳሉ ያረጋገጡ እንደሆኑና ያሉንን እምቅ ሀብት በአግባቡ ጠብቀንና ተንከባክበን በማቆየት የአገር ውስጥና ዲያስፖራውን በማስተባበር በሚገባ በማልማት ብዙ ቢሊዮን ዶላሮችን ማስገኘት እንደሚቻል ተናግረዋል::

የቀድሞ የሶዶ ወረዳ የባህል ቱሪዝም ኃላፊ የነበሩት አቶ አዳነ ተሰማ እንደተናገሩትም የዓለም ቱሪዝም ቀን መሠረት ተደርጎ ከአዲስ አበባ ከ 11 ክፍለ ከተማ የተውጣጡ የባህል ቱሪዝምና ኪነ ጥበብ ቢሮ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ከ250 በላይ ቱሪስቶች ጥያ መካነ ቅርስን የጎበኙ ሲሆን በጉብኝቱም የጥያ መካነ ቅርስ የዓለም ቅርስ ሳይት እንደመሆኑ መጠን ከዘርፉ የሚገኙ የቱሪዝም ገቢዎች የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም መስራት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል።

የሀገር ውስጥ ቱሪስቶቹ የመምጣታቸው ምክንያት በባለፈው የጥያ መካነ ቅርስ ግቢ የተጀመረው የአዳብና ፌስቲቫል ተቋሙ የአዲስ አበባ ባህል ቱሪዝም ኪነጥበብ ቢሮ ጋር በፈጠረው የሁለትዮሽ ግንኙነት መሆኑን ጠቁመው በተለይም ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የሀገር ውስጥ ጎብኚ ቁጥሮች በተሠሩት ፕሮሞሽን መሠረት ቁጥሮቹ ጨምረዋል ብለዋል።

የዛሬው የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ የገቢ ምንጮች ከመጨመሩ ባሻገር በዕደ ጥበብ የተደራጁ ቡድኖች ምርታቸውንም ገበያ ላይ በማቅረብ ከቱሪዝም ዘርፉ የገበያ ትስስሩ አጠንክሮላቸዋል ብለዋል ሲል የዘገበው የሶዶ ወረዳ መ/ኮ/ጉ/ጽ/ቤት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *