እየተቀዛቀዘ የመጣውን የጤና ኤክስቴሽን የአገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል ህብረተሰቡን ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰራ የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በሚቀጥሉት 15 አመታት ተግባራዊ የሚደረግ የጤና ኤክስቴሽ መርሃ ግብር ፍኖተ ካርታ አዘገጃጀትና አተገባበር ላይ በዞኑ ለሚገኙ የጤና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በወልቂጤ ከተማ ተሰጥቷል፡፡

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ የበሽታ መከላከልና የጤና ማበልጸግ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አመነ ወልዴ በስልጠናው ተገኝተው እንደገለጹት በሀገሪቱ የጤና ኤክስቴሽን መርሃ ግብር አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በ2012 ዓ/ም 15 አመት የሞላው በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ወቅቱ የሚፈልገውን የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት እንደማይችል በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያመላክቱ ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም በሚቀጥሉት አስራ አምስት አመታት ለህብረተሰቡ የተሻለ የጤና አገልግሎት በቅርብ ርቀት መስጠት የሚያስችል የጤና ኤክስቴሽን መርሃ ግብር ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ አመነ ወልዴ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ጤና ኬላዎች ለአገልግሎት በሚያመች መልኩ ከጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ያላቸውን ርቀት በመለየትና በሶስት ደረጃ በመከፋፈል ወደ ትግበራ እንደሚገባ የገለጹት አቶ አመነ ወልዴ ተጨማሪ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ግንባታዎች በመገንባት፣የባለሙያዎች ክህሎት በማሻሻል፣ ተጨማሪ ባለሙያዎች በመመደብ፣ የጤና ግብዓትና መሰረተ ልማት በማሟላት የህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ይሰራል ብለዋል፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የእነሞርና ኤኔር ወረዳ የጤና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ዘፕር እና የእዣ ወረዳ የጤና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መሀመድ ሰይድ ይገኙበታል፡፡

ሁለቱም ስልጠናውን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት አዲሱ የጤና አክስቴሽን መርሃ ግብር ፍኖተ ካርታ እየተቀዛቀዘ የመጣውን የጤና አክስቴሽን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እንደሚረዳ ግንዛቤ ማግኘታቸውና ለተግባራዊነቱም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

አክለውም የጤና አክስቴሽን ፍኖተ ካርታው ሙሉ በመሉ ተግባራዊ ሲደረግ አሁን በቤት የሚወልዱ እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ በማድረግ በወሊድ ምክንያት የሚደርስባቸውን የጤና እክል እና የጨቅላ ህጻናት ሞት ለመቀነስ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው በዞኑ ከሚገኙ ሁሉም ወረዳዎችንና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የጤና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊዎች ተሳታፊ ነበሩ ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *