እምድብር ከተማን ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ማጠናከር እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ አስታወቀ።

ግን

በከተማው ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የመንገድ፣ የዲችና የመንገድ ከፈታ ስራዎች ተመረቁ።

የጉራጌ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምራት ውድማ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት በዞኑ የሚገኙ ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።

በ2015 በጀት አመት 11 ከተሞች እውቅና እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር የሌሎች ነባር ከተሞች ፕላን በመከለስ እንዲስፋፉ እየተሰራ መሆኑን አቶ ታምራት ገልጸዋል ።

በዞኑ የማስፋፊያ ስራዎች ከሚከናወንባቸው ከተሞች አንዱ የእምድብር ከተማ አስተዳደር መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታ፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍና የጎርፍ መውረጃ ዲቾች ተገንብተዋል ብለዋል።

በመሆኑም ለምረቃ የበቁ እነዚህ መሰረተ ልማቶች ዘላቂ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የከተማው ነዋሪዎች አስፈላጊውን ክብካቤ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አቶ ታምራት አስገንዝበዋል።

የእምድብር ከተማ ከንቲባ አቶ ግንባሩ በርጋ በበኩላቸው የከተማው እድገት ለማፋጠን በ2015 በጀት አመት ልዩልዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ከማከናወን ባለፈ ፕሮጀክቶቹ በጥራትና በፍጥነት ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ተደርጓል ብለዋል።

እንደ ከንቲባው ገለፃ የመሰረተ ልማቶቹ መስፋፋት የነዋሪዎቹን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከማቀላጠፍ ባሻገር የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማነቃቃት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

ከተማው ከአዲስ አበባ ያለው ቅርበት፣ የመሰረተ ልማት መስፋፋትና የሰለጠነ የሰው ሀይል መኖሩ ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ እንደሚያደርገው የተናገሩት ከንቲባው መዋዕለንዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ከ40 ሄክታር በላይ መሬት ከይገባኛል ነጻ በማድረግ ማዘጋጀት ተችሏል ብለዋል።

የከተማው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ስራአስኪያጅ አቶ ሲሳይ ተክሌ በበኩላቸው በከተማው ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የዲች፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍና የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታ ስራዎች የከተማው እድገት ለማፋጠን ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ሲሆን ወጪው በማቺንግ ፈንድ መሸፈኑንም አስረድተዋል።

ከተማው ውብ፣ ማራኪና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎ ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ሲሳይ ከመሰረተ ልማት ስራዎች ባሻገር በችግኝ ተከላና ክብካቤ ስራ ያላቸውን ተሳትፎ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በከተማው መዋዕለነዋያቸውን የሚያፈሱ ባለሀብቶች ቁጥር እያደገ ሲሆን በበጀት አመቱ የ12 ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ በማጽደቅ ወደ ክልል መላኩን አቶ ሲሳይ ተናግረዋል።

አቶ ወልደ ሚካኤል ደረጃ፣ አቶ ደገሙ ጋሩማ እና ወይዘሮ በዝናሽ አንትዋን የእምድብር ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ባለፉት አራት አመታት የተሰሩ መሰረተ ልማቶች በከተማው እድገት ላይ ተስፋ እንዲሰንቁ አድርጓቸዋል።

እንደነዋሪዎቹ ገለፃ የከተሞች እድገት ለማፋጠን የህብረተሰቡን ተሳትፎ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ከተማው ለማሳደግ በገንዘብ፣ በጉልበትና በእውቀት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል።

የከተማው ፕላን ተጠብቆ እድገቱ እንዲፋጠን ወጣቶችና ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ከመንግስት ጎን ሆነው ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።

በመሆኑም የዞኑ ተወላጆና ሌሎች ባለሀብቶች በከተማው መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈሱ መልዕክት አስተላልፈዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *