ኢትዮጵያ ያላትን የቡና እምቅ አቅም በሳይንስ ተደግፎ ሀገሪቱ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን የዘርፉ የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑን የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን የቡና እምቅ አቅም በሳይንስ ተደግፎ ሀገሪቱ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን የዘርፉ የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑን የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ የቡና ሳይንስ ማህበር አመታዊ ኮንፈረስ በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ማካሄድ ጀምሯል፡፡

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ ኮንፈረሱ ላይ እንዳሉት በሀገሪቱ ቡና በየዕለቱ ከምንጠቀመው መሰረታዊያን ውስጥ የሚመደብ፣ በማንኛው ሰው ቤት የሚዘጋጅ፣ እንግዳ የምንቀበልበት፣ የኢኮኖሚ የገቢ ምንጭና ዜጎች ቡና እየጠጡ የርስ በርስ ትስስራቸው እንዲጠናከር የሚያስችል አረንጓዴ ወርቅ ነው፡፡

የጉራጌ ዞን በሀገሪቱ ቡና አብቃይ ከሆኑ አካባቢዎች መካከል አንዱ ሲሆን ከ49 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በቡና ተክል እንደተሸፈነና የሚመረተው ቡና በጣም ጥራት ያለው በተለያየ ሰንሰለት ገበያ እየቀረበ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚሸጥ ምክትል አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡

ሆኖም አርሶ አደሮቹ ቡና የሚያመርቱት በባህላዊ መንገድ በመሆኑ በሚፈለገው ልክ ውጤታማና ተጠቃሚ ያለመሆናቸውን ገልጸው ለዚህም ምክንያት በሽታን መቋቋም የሚችሉ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች እጥረትና የቴክኒክ ድጋፍ ማነስ እንደሆነ አቶ አበራ አብራርተዋል፡፡

በቀጣይ የቡና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ አርሶ አደሩ በቀጥታ የውጭ ገበያ አቅርቦ በመሸጥ ተጠቃሚ የሚሆኑበትና ሀገሪቱ ከዘርፉ የሚጠበቀውን የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ለመስራት የሚያስችል ግብዓት ከኮንፈረንሱ ይገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት ደ/ር ፋሪስ ደሊል በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያላትን የቡና እምቅ አቅም በሳይንስ ተደግፎ ሀገሪቱ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን የዘርፉ የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቡና በማህበረሰቡ ውስጥ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር ረገድ ሰፊ ሚና ያለው ከሀገራችን አልፎ በአለም ደረጃ የቡና አዘገጃጀቱ ቢለያይም ሰዎች ቡና እየጠጡ ሀሳብ በመለዋወጥ እንዲወያዩ መድረክ የሚፈጥር ከፈጣሪ የተሰጠን ፍሬ እንደሆነ ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቡና ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ሆኖ ለዘመናት የዘለቀ የኢኮኖሚ ዋልታ ቢሆንም ሀገሪቱ ካላት እምቅ አቅም አኳያ በደንብ ያልተጠቀመችበት እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ለቡና ምርት ምቹ ስነምህዳር ያለው ቢሆንም የተሻሻሉ ዝርያዎች እጥረት፣ ልዩ ልዩ በሽታዎች ተጽዕኖ፣ በቂ የሆነ ሙያዊ ድጋፍ ማነስና በሌሎች ምክንያቶች በሚፈለገው ልክ አርሶ አደሩ ማምረት ያለመቻሉን የገለጹት ደ/ር ፋሪስ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ አነዚህ ችግሮች ለመቅረፍ እንዲረዳ የችግኝ ጣቢያዎችን በማቋቋም ምርምር እያደረገ ይገኛል፡፡

በኮንፈረሱ የሚቀርቡ ሳይንሳዊ የምርምርና የቴክኖሎጂ ውጤቶች በአለም አቀፍ ደረጃ የሀገሪቱ የቡና ኢንዱስተሪ በዘላቂነት እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል የሚያመላክት የቀጣይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ደ/ር ፋሪስ ደሊል ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ሳይንስ ማህበር ፕሬዝዳንት ፕ/ር ገዛኸን በሬቻ ኮንፈረሱን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት በቡና ላይ የተካሄዱ የተለያዩ የምርምር ስራዎችና የተሻሉ ልምዶች ቀርበው ለሀገሪቱ ፖሊሲ አውጭዎች የሚሆን ግብዓት በመስጠጥ ምሁራን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ካነጋገርናቸው የኮንቨረሱ ተሳታፊዎች መካከል በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ ደ/ር ተስፋዬ ሽምብር እንደተናገሩት ቡና ለኢትዮጵያዊያን እንደባንዲራችን ነው፡፡ ምክንያቱም የአረቢካ ቡና መገኛና እምቅ አቅምም ያለው በኢትዮጵያ ሲሆን የአየር ንብረቱም ለቡና እጅግ ተስማሚ ቢሆን በብዛት ማምረት አልተቻለም፡፡

እንደዚህ አይነት ኮንፈረሶች መካሄዳቸው በሳይንሳዊ ምርምርና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎቸ በማፍለቅ የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *