ኢትዮጵያዊነት የሚንጸባረቅባት የአብሬት ሀድራ በማልማትና በአግባቡ ጠብቆ ለትዉልድ ለማስተላለፍና ለማሰቀጠል የሁሉም ሰዉ ሀላፊነት ሊሆን እንደሚገባም ተገለጸ።

በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ በአብሬት ቀበሌ አመታዊ መዉሊድ በዓል በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

የአብሬት ሀድራ በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ አብሬት ቀበሌ ከእምድብር ከተማ መስተዳድር በስተ ደቡብ ምእራብ በ18 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ የእስልምና ሀይማኖት ት/ት መስጫ ማእከል ነዉ።

በርካታ ቁጥር ያላቸዉ የእስልምና እምነቱ ተከታዮችና የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት መዉሊድ በአብሮነት ፈጣሪን በማወደስ እየተከበረ ይገኛል።

የሀድራዉ ህሊፋ ልጅ ሁስኒ ሰኢድ ኒቅማስ እንዳሉት በአብሬት አመታዊ መዉሊድ የሚያከብሩ ምዕመናን ቁጥር በየጊዜዉ እየጨመረ ይገኛል።

መዉሊዱን ለማክበር በመላዉ ኢትዮጵያ የሚገኙ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች አብሬት ድረስ መጥተዉ በአንድነት ፈጣሪን በማወደስ እለቱን በጋራ ያከብሩታል ብለዋል።

በየአመት የሚከበረዉ የመዉሊድ በአል ዘር ቀለም የማይለይበት፣ ያለዉ ለሌለዉ እየሰጠ በፍቅር መዉሊዱን በአንድነት የሚከበር እንደሆነም አመላክተዋል።

መዉሊድ በሚከበርበት አብሬት ቀበሌ በልማቱ ማለትም በመንገድ ፣ በንጹህ መጠጥ ዉሃ መብራትና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ክፍተት መኖሩም አንሰተዉ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ መላዉ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ፣ምዕመናንና መንግስት ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባም አስረድተዋል።

ሀድራዉ የቱሪስት መስህብ ሲሆን በዚህ መዉሊድ በርካታ ቁጥር ያላቸዉ የማህበረሰብ ክፍሎች በተለያዩ የንግድ ስራ ተሰማርተዉ የአመት ገቢያቸዉን የሚያገኙበት እንደሆነም አብራርተዋል።

ሀድራዉ በተገቢዉ በማልማትና የቱሪስት መስህብ እንዲሆን የመሰረተ ልማት ችግሮች መቅረፍ እንደሚገባም አመላክተዉ መዉሊዱን ለመታደም የሚመጡ ምዕመናኖች ነብዩ መሀመድ(ሰ .ዐ.ወ ) በማወደስና ትልልቅ መሻሂኮችን በማክበርና በሀይማኖታዊ ሁነቶች በድምቀት ይከበራል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊነት የሚንጸባረቅባት የአብሬት ሀድራ በማልማትና በአግባቡ ተጠብቆ ለትዉልድ ለማስተላለፍና ለማሰቀጠል የሁሉም ሰዉ ሀላፊነት ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።

በሀድራዉ በአመት ረመዳንና ከረመዳን ዉጪ አመቱን ሙሉ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተዉጣጡ ወገኖች ሀይማኖታዊ ትምህርት የሚማሩበት ትልቅና ታሪካዊ ሀድራም እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ሀጅ መሀመድ አብልቃዲስ በበኩላቸዉ በአብሬት መዉሊድ የሚታደሙ ምዕመናን በአንድ ላይ በመሆን ጀመዓ ሰላት በመስገድ ለሀገር ሰላም ዱአ በማድረግ እንዲሁም ሁሉም ካለዉ ላይ በማካፈል በአብሮነት የሚያከብረዉ መዉሊድም እንደሆነም አስታዉቀዋል።

በተለያዩ ንግድ ስራ የተሰማሩ አንዳንድ አሰተያየት ሰጪዎች እንዳሉት በየአመቱ የአብሬት መዉሊድ ለማክበር የሚመጡ እንግዶች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

በአመት አንድ ጊዜ በድምቀት በሚከበረዉ የአብሬት መዉሊድ ለመታደም ለሚመጡ እንግዶች የምግብና የተለያዩ ቁሳቁሶች በማቅረብ ገቢያቸዉን እያሳደጉም እንደሆነም አመላክተዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *