አዲሱ ዴልታ የኮሮና ቫይረስ በሽታ ለመከላከል የክትባት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑ የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ ለሚገኙ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና ለትምህርት ሴክተር ባለድርሻ አካላት የኮቪድ 19 ቫይረስ መከላከል ክትባት በዛሬ እለት በወልቂጤ ከተማ ተሰጥቷል።

አዲሱ ዴልታ የኮሮና ቫይረስ በሽታ በከፍተኛ ደረጃ እየተዛመተ እንደሆነም ማህበረሰቡ አዉቆ ማስክ በማድረግ ፣ የእጅ ንጽህና በመጠበቅና ርቀትን ጠብቆ በመንቀሳቀስ እራሱንና ቤተሰቡን ከቫይረሱ ሊከላከል እንደሚገባም ጥሪ ቀርቧል።

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸምሱ አማን እንዳሉት እንደ ሀገር ኮቪድ 19 መከላከል ላይ ከፍተኛ መዘናጋት እንዳለ ተናግረው ህብረተሰቡ እንደመጀመሪያዉ ደንግጦ ርቀቱን የመጠበቅ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክና ሳኒታይዘር የመጠቀምና የእጅ ንጽህና መጠበቅ ሁኔታ ከመዘናጋት ወጥቶ አሁን ትኩረት ሰጥቶ ሊተገብራቸው ይገባል ብለዋል።

አሁን ላይ የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ መኖሩና የኮቪ 19 በሽታ እራሱን የሚቀያየርበት ሁኔታ እንዳለ ያስታወቁት ኃላፊ አዲሱ ዴልታ የኮሮና ቫይረስ ከዚህ ቀደም በሀገራችን ያልታየ በሽታ እንደነበረና አሁን ላይ ወደ ሀገራች መግባቱም አብራርተዋል።

አዲሱ ዴልታ ፕላስ ዝርያዎች በአዉሮፖና አሜሪካ ሀገሮች አካባቢ እየታዩ ያሉበት ሁኔታ መኖሩም ተናግረዉ ይህ አስጊና አስቸጋሪ በሽታ እንደኛ ሀገር የኢኮኖሚና አሁን እንዳለንበት ሁኔታ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው።

ሀገሪቱ አሁን ላይ የጸጥታ ችግር ዉስጥ እንደሆነችም አመላክተዉ በሽታዉ የበለጠ ከተዛመተ የኢኮኖሚ የመዋዠቅ ችግር እንደሚኖርና ህብረተሰቡ የጤና ችግር ዉስጥ ቢገባና በመንግስት እየገጠመዉ ያለዉን የዉጭ ምንዛሬ ምክንያት ለመተንፈሻ አካላቶች የምንጠቀማቸዉን ማቴሪያል ለማስገባት ከፍተኛ ችግር ዉስጥ ልንገባ እንችላለን ብለዋል።

በሀገሪቱ ወደ 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ህዝብ የኮሮና ቫይረስ ተመርምረዉ ከነዚህም ዉስጥ ወደ 3 መቶ 62 ሺህ አካባቢ የሚሆኑ ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱና ከ6ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸዉ ማለፉም አስታዉሰዋል።

በዞኑ ከ19 ሺህ 8 መቶ 82 የህብረቸሰብ ክፍሎች ምርመራ ተደርጎላቸዉ ከነዚህም ዉስጥ 1 ሺህ 8 መቶ 64 የሚጠጉ ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል ያሉት ኃላፊዉ በዚህም ወደ 39 የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸዉ ማለፉም አስታዉሰዉ በዞኑ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገቢዉ በመከተብ ርቀታቸዉን በመጠበቅና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በማድረግ በሽታዉን መከላከል እንዳለባቸዉም አሳስበዋል።

የወልቂጤ ከተማ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሙና ሸሪፍ እንዳሉት የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን ከገባ ሁለት አመት እንደሆነና በከተማዉ ህብረተሰቡ ላይ መዘናጋቶች ይስተዋላል።

አሁን ላይ የቫይረሱ ስርጭት ይበልጥ ለመከላከል በየትምህርት ተቋማት፣ በገበያዎችና በከተማዉ በተለያዩ ቦታዎች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየሰሩ መሆነም አመላክተዋል።

በከተማ ዉስጥ በሚገኙ ጤና ተቋማት ህብረተሰቡ ለአገልግሎት ሲመጣ ማስክ እንዲጠቀሙ የማድረግና ርቀትን ጠብቀዉ የትኛዉም አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሆነም አብራርተዋል።

ዴልታ የሚባለዉ አዲሱ የኮሮና ቫይረስ በሽታ አስጊ እንደሆነም ያመላከቱት ኃላፊዋ በማረሚያ የሚገኙ 6 መቶ ወገኖች ክትባት መከተባቸዉና ከዞኑ ጤና መምሪያ ጋር በመናበብ ለእያንዳዱ እስረኛ ማስክና ሳኒታይዘር ማቅረብ መቻላቸዉም አስረድተዋል።

ክትባት ከወሰዱ አመራሮች መካከል አቶ ተመስገን ገብረመድን እንዳሉት የኮቪድ 19 በሽታ መድሀኒት ያልተገኘለት በሽታ ሲሆን ህብረተሰቡ በሽታዉ እንዳይዘዉ ክትባት በአግባቡ መዉሰድ እንዳለበት ተናግረዋል።

በዞኑ በሁለም አካባቢዎች ላይ ወረርሽኙ ተከሰተ በተባለበት ወቅት በማህበረሰቡ የሚታዩ መደናገጦች ፣ ስሜቶችና በሽታዉን ለመከላከል ያደርጉት የነበሩ ጥንቃቄዎች አሁን ላይ ችላ እንደተባሉም አብራርተዋል።

በዛሬዉ ዕለት 106 አመራሮችና የት/ቤት ባለድርሻ አካላት አዲሱ የዴልታ ቫይረስ መከላከላከያ ክትባት መዉሰዳቸዉም ታዉቋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *