አካባቢያዊም ሆነ ሀገራዊ ሠላም እንዲጠበቅ በማድረጉ ረገድ የሴቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ አስታወቀ

በቀጣይ “የኢትዮጵያን ሠላም አስጠብቃለሁ ለልጄም ምንዳን አስረክባለሁ” በሚል መሪ ቃል ለሚካሄደው ዞናዊ የሴቶች የንቅናቄ መድረክ አስመልክቶ ለሚመለከታቸው አካላት በዛሬው እለት ኦረንቴሽን ተሰጥቷል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት አስተባባሪነት “የኢትዮጵያን ሠላም አስጠብቃለሁ ለልጄም ምንዳን አስረክባለሁ” በሚል መሪ ቃል ለሚካሄደው ዞን አቀፍ ንቅናቄ ከዞኑ፣ ከወረዳና ከተማ አስተዳደሮች ለተገኙ የሴቶች ሊግ አስተባባሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በንቅናቄው አተገባበር ዙሪያ ኦረንቴሽን በዛሬው እለት ተሰጥቷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል እንዳሉት ሴቶች አካባቢያዊም ሆነ ሀገራዊ ሠላም በማስጠበቁ ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው።

በተለይም ንቅናቄው ሴቶች ለሠላም መጠበቅ ሚናቸው ይበልጥ እንዲጎላ ለማድረግና እንዲሁም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም በፖለቲካው ዘርፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ነው ብለዋል።

በዚህም በአተገባበሩ ዙሪያ ኦረንቴሽን የተሰጣቸው አካላትን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ለውጤታማነቱ በትኩረት መስራት ይኖርባቸዋል ሲሉም አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ት ሲቲ አብራር የንቅናቄው ሰነድ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ንቅናቄው ሴቶች ተጠቃሚነታቸው ለማሳደግ ብሎም ችግሮቻቸው በግልጽ እንዲናገሩ የሚደረግበት ነው።

የሴቶች አደረጃጀት ለሴቶች ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን መሆን አጋዥ ነው ያሉት ኃላፊዋ ንቅናቄውም ይህንኑ ውጤታማ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

ፓርቲው ለሴቶች ተጠቃሚነት አበክሮ እየሰራ መሆኑንና ዞን አቀፍ ንቅናቄውም ከቀበሌ ጀምሮ እንደሚካሄድም ተናግረዋል።

ሴቶች ለሠላሙ መጠበቅ ያላቸውን ከፍተኛ ሚና ከማሳየት ባለፈ በግብርናው፣ በሌማት ትሩፋትና በሌሎችም ዘርፎች የተሰሩ የልማት ስራዎች ምርጥ ተሞክሮ እንዲጎበኙ ይደረጋል ብለዋል።

ሁነቱ ሴቶችን የሚጠቅሙ ልዩ ልዩ ተግባራት የሚከናወንበት መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም አካል ለንቅናቄው ውጤታማነት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግም ኃላፊዋ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኦረንቴሽኑ ተሳታፊዎች እንዳሉት ንቅናቄው የሴቶች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ የሚያግዝ በመሆኑ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ሲል የዘገበው የዞኑ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *