አካል ጉዳተኞች የ”እችላለሁ” መንፈስ በመላበስ በተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች አርአያነት ያለው ተግባር ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።


በአለም ለ32ኛ እንዲሁም በሀገራችን ለ31ኛው ጊዜ የአካል ጉዳተኞች ቀን “ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት ትርጉም ያለው ትብብር” በሚል መሪ ቃል በምሁር አክሊል ወረዳ ሀዋሪያት ከተማ ተከበረ።

በአለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጉራጌ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ መኩሪያ ተመስገን አካል ጉዳተኞች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻቸው ለመቅረፍ መምሪያው እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በበጀት አመቱ ከድህነት ወለል በታች ለሚገኙ 641 አካል ጉዳተኞች የምግብ፣ የአልባሳት፣ የገንዘብና ለእርሻ ስራ አገልግሎት የሚሰጡ መሳሪያዎች ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

እንደ አቶ መኩሪያ ገለጻ ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ግንባታ ሲያከናውኑ አካል ጉዳተኞች ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ እየተሰራ ይገኛል።

በበጀት አመቱ ከቼሻየር ኢትዮጵያ፣ ከአጣጥ ሆስፒታል፣ ከባለሀብቶች ፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከመንግስት ጋር በመቀናጀት ለ36 አካል ጉዳተኞች ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ እንደተደረገላቸው አቶ መኩሪያ ገልጸዋል።

አካል ጉዳተኛ ህጻናት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይርቁ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ መኩሪያ ለ11 ሺህ 649 ህጻናት የደንብ ልብስና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን አራት ተማሪዎች ዊልቸር ድጋፍ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።

የአካል ጉዳተኞች ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲከበርላቸውና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ለማረጋገጥ በዞኑ በሚገኙ መዋቅሮች የአካል ጉዳተኞች ማህበርት የተቋቋሙ ሲሆን ማህበራቱ በሰው ሀይል እና በቁሳቁስ ለማሟላት 515 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

የምሁር አክሊል ወረዳ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ከበደ ሳህሌ እንደተናገሩት አካል ጉዳተኝነት ሰርቶ ራስንና ሀገርን ከመለወጥና የተለያዩ በጎ ተጽእኖዎች ከመፍጠር የማያግድ በመሆኑ አካል ጉዳተኞች በተሰማሩባቸው ዘርፎች ውጤታማ ስራ በመስራት አርአያ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

የጉራጌ ዞን አካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አብይ ጀማል በበኩላቸው አካል ጉዳተኞች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸው ለመቅረፍ ከመንግስት ጋር በመሆን እየተሰራ ይገኛል።

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ በየመዋቅሩ የተቋቋሙ የአካል ጉዳተኞች ማህበር ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም በቅንጅት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች እንደተናገሩት አካል ጉዳተኞች በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተሳትፎ እና አበርክቶ የላቀ እንዲሆን መንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

አካል ጉዳተኞች በተሰማሩባቸው አካባቢዎች ምርታማ እንዲሆኑ ምቹ የስራ አካባቢ ሊፈጠረላቸው ይገባል ያሉት ተሳታፊዎቹ መንገድና ህንጻዎች ሲገነቡ አካል ጉዳተኞች ታሳቢ ሊደረጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአካል ጉዳተኞች መሰረታዊ ችግሮች በመንግሥት ብቻ የሚቀረፉ ባለመሆናቸው ባለሀብቶች፣ አጋር ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸው እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

አያይዘውም ተሳታፊዎቹ በየ አመቱ የሚከበረው የአካል ጉዳተኞች ቀን ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በአካል ጉዳተኞች ላይ ያላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ ከመቅረፍ ባለፈ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ እድል የሚፈጥር በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *