አካል ጉዳተኞች በዞኑ በሁሉም ዘርፍ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።


“የአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት ትርጉም ያለው ትብብር” በሚል መሪ ቃል ዞናዊ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ህብረት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ተመሰረተ።

የጉራጌ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ፈቀደ በምስረታው ተገኝተው እንዳሉት አካል ጉዳተኞች መደገፍ በስጋ ብቻ ሳይሆን በነብስም ጽድቅ የሚገኝበት በመሆኑ እነዚህ ወገኖች መደገፍ ላይ ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ ይገባል።

አካል ጉዳተኝነት ወደውና ፈቅደው ያመጡት ሳይሆን ሰዎች በተለያየ ምክንያት የሰውነት ክፍላቸውን የአካል ጉዳት ሊገጥማቸው ይችላል ያሉት ኃላፊው የእነዚህ ህብረተሰብ ክፍሎችን እውቀታቸው፣ ሞያቸውና ክህሎታቸው በተገቢው መጠቀም እንደሚገባ ገልጸው የሀገር ብልጽግና ለማረጋገጥ የሁሉም ዜጎች እኩል ተሳታፊነት ማሳደግ ይገባልም ብለዋል።

በማህበረሰቡ ዘንድ ከዚህ በፊት አካል ጉዳተኞችን በተለያየ መልኩ የማግለል አስተሳሰቦች እንደነበረ ጠቅሰው አሁን ላይ ይህ አስተሳሰብና አመለካከት እየተቀረፈና እያደገ በመምጣቱ ህብረተሰቡ ከእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ብዙ እውቀትና ልምድ ማግኘት እንደሚችል እያመነ መምጣቱንም ጠቁመዋል።

በየአካባቢው ሰው ሊደርስላቸው ያልቻሉ አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን ያነሱት አቶ ደሳለኝ እነዚህ ወገኖች ለመደገፍ፣ ለማበረታትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመንግስት በተለያየ መልኩ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

ህብረቱ መመስረቱ ተንቀሳቅሰው ለሚሰሩ አካል ጉዳተኞች ብቻ ሳይሆን አስታዋሽ ላጡትም ጭምር ጠበቃ የሚሆንና ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥዘርፍሆን እንደሚገባ ጠቅሰው የዞኑ አስተዳደር የሚያደርጋቸውን እገዛና ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ መኩሪያ ተመስገን በበኩላቸው እንደ ሀገር የወጡ መመሪያዎችና ደንቦች ተግባራዊ ለማድረግ አካል ጉዳተኞች በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚ ዘርፎች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑና መብቶቻቸው እንዲከበር ለማድረግ መምሪያው እየሰራ ይገኛል።

ሁሉም አካባቢዎች ከተናጥል በመውጣት በህብረት በመደራጀት የአካል ጉዳተኞች መብት ከማስከበር ባለፈ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆንና በፖለቲካዊ ዘርፍ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከማድረጉም ባሻገር በየደረጃው ያሉ ማህበራት እንዲጠናከሩ የህብረቱ መመስረት ወሳኝ ነው ብለዋል።

እንደ ዞንና ሀገር በዘርፉ በርካታ ስራዎች እየተሰራ ሲሆን በማህበር በመደራጀት የአካል ጉዳተኞች የግንዛቤና የአመለካከት ክፍተቶችንና ያልተቀረፉ ችግሮችን ለመቅረፍ በየደረጃው ያለው ማህበር ማጠናከር ይገባል። ለዚህም መምሪያው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን አካል ጉዳተኞች ማህበራት ህብረት ፕሬዝዳንት አቶ አብይ ጀማል የህብረቱ አላማ የአካል ጉዳተኞች መብቶችና ደህንነቶች እንዲጠበቅ፣ በሁሉም ዘርፎች ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥና የማህበረሰቡን ንቃተ ህሊና ለማሳደግ ነው።

የአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በዞኑ እየተሰሩ ያለ ስራዎችን የበለጠ በማጠናከር በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች እኩል ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማሳደግ ሁሉም አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የህብረት ምስረታው እንዲሳካ እገዛ ላደረጉ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የአካል ጉዳተኞች ማህበር ህብረት በወጣው መተዳደሪ ደንብ ላይ ተወያይተው አጽድቀዋል።

በመጨረሻም የአካልጉዳተኞች ማህበር ህብረት ባለ 8ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *