አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ በአንድ ሴት በአንድ ወንድ በሚል መሪ ቃል ዞን አቀፍ ንቅናቄ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ተካሄደ።

ሴቶችና ወጣቶች በትምህርት ዘርፍ በተለይም የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል እየተሰራ ባለው ስራ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ጥሪውን አቅርቧል።

ጉራጌ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ክብሩ ፈቀደ በመድረኩ ባስተላለፊት መልዕክት ትምህርት ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝና ለሌሎች እድገቶች ቁልፍ መሳሪያ መሆኑ መላው ህብረተሰብ በተለይም ሴቶችና ወጣቶች ተገንዝበው በዘርፊ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እብዳለባቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የተሟላ ስብዕና የተላበሰና በእውቀቱ የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር ህብረተሰቡ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ያብራሩት አቶ ክብሩ ፈቀደ አንደ ሀገር አቀፍ የገጠመው የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ፈጥኖ ለማሻሻል አስፈላጊ የመማሪያ ቁሳቁሶች በተለይም መማሪያ መጽሐፍት ማሟላት ግድ የሚል በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ወጣቶችና ሴቶች በንቃት ሊሳተፉ ይገባል ብለዋል።

በጉራጌ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አመተሩፍ ሁሴን የሴቶችና የወጣቶች አደረጃጀቶች ከአመራሩ ጋር ተቀናጅቶ በሰላም፣ በልማት፣በማህበራዊ አገልግሎቶች በሳታፍ አለባቸው።

ሴቶችና ወጣቶች በኢኮኖሚያዊ፣ በፓለቲካዊና በማህበራዊ ዘርፎች ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የሴቶችና የወጣቶች ሊጎች የተጣለባቸው ከፍተኛ ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ተብለዋል ።

በትምህርት ልማት ዘርፍ የገጠመው የተማሪ ውጤትና የስነ ምግባር ችግር ለማሻሻል ሴቶችና ወጣቶች ከመላው ህብረተሰብ ጎን ተሰልፈው አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ በሚል የተጀመረው ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን ሊጎች ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

በጉራጌ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የሴቶች ሊግ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሪት ሲቲ አብራር በትምህርት ዘርፍ የገጠመው ስብራት ለማከም ለትምህርት አመራርና ለትምህርት ቤት ማህበረሰብ ብቻ የሚተው ጉዳይ እንዳልሆነ ገልጸው ሴቶችና ወጣቶች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው ማገዝ አለባቸው ብለዋል።

የዞኑ ሴቶችና ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ፣ በህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በሌማት ቱሩፋት፣ በበጎ ፈቃድ እና በመሳሰሉት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን የገለጹት ወ/ሪት ሲቲ አብራር አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ ከማዳረስ ባለፈ በዘርፊ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በማረም ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ ስራዎችን መስራት ይቻላል ተብለዋል።

በጉራጌ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መኪ ሁሴን በበኩላቸው የመማሪያ መጽሐፍት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ አንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ በሚል መሪ ቃል የተጀመረውን ዞናዊ የሃብት አሰባሰብ ስራ በቅንጅት በመፈጸም በሁለቱም የሊጎች አደረጃጀት፣ አባላትና ደጋፊ 13 ሚሊዮን ብር በመሠብሰብ ድርሻቸውን መወጣት ችለዋል ብለዋል ፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ሴቶችና ወጣቶች በአረንጓዴ አሻራ፣ በህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በሌማት ቱሩፋት፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እና በመሳሰሉ የልማት ተሳትፎ ያገኙትን ልምድ በመጠቀም አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ በአንድ ሴት በአንድ ወንድ በሚል ሀሳብ ወደ ተግባር መግባታቸውና ውጤትም እያስመዘገቡ መሆኑ አብራርተዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *