አንትሮሽት የእናቶች በዓል በይበልጥ እንዲከበርና እንዲተዋወቅ በማድረግ ለሃገርና አለማቀፋዊ የቱሪዝም መስህብ እንዲሆን እንደሚሰራ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

ጥር 18/2015 ዓ/ም

አንትሮሽት የእናቶች በዓል በይበልጥ እንዲከበርና እንዲተዋወቅ በማድረግ ለሃገርና አለማቀፋዊ የቱሪዝም መስህብ እንዲሆን እንደሚሰራ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

ዞን አቀፍ የአንትሮሽት “የእናቶች በዓል” በጉራጌ ዞን በቸሃ ወረዳ በመገናሴ ቀበሌ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበዓሉ ተገኝተው እንዳሉት ” እናት የቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ሁሉ አቀፍ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት ባሻገር የሀገር ምሰሶ እንደሆነች ይታወቃል።

የእናትን ውለታ የተረዳው የጉራጌ ማህበረሰብ ከጥንት ጀምሮ አለም ስለ እናቶችም ሆነ ስለሴቶች መብትና ነፃነት ማሰብ ባልጀመረበት ዘመን ላይ የለፋችና የደከመችን እናት ክብር ለመስጠት ያከበር ነበር ብለዋል ።

አንትሮሽት መቼና እንዴት ተጀመረ የሚለው እድሜ ጠገብ በርካታ ታሪካዊ ዳራ ያለው መሆኑን አባቶች ቢያስረዱም የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ባጠኑት ጥናት መሰረት ከ2 መቶ 50 እስከ 3 መቶ አመትና በላይ እንደሆነና በዘርፉ ተጨማሪ ጥቅል ጥናትና ምርምር መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል።

አንትሮሽትን በቀጣይ በላቀ ደረጃ ከፍ እንዲልና ሃገራዊና አለማቀፋዊ ይዘቱን ጠብቆ የባለቤትነት መብት በማረጋገጥ እናቶችን በየአመቱ እንዲያከብሩት ከማድረግ ባለፈ ለሃገርና አለማቀፋዊ የቱሪዝም መስህብ እንዲሆን የዞኑ አስተዳደር የበኩሉን ድርሻ አንደሚወጣ ገልጸዋል።

የኢፌድሪ ሴቶች ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስተር ዴኤታ አማካሪ ክብርት ዘቢዳር ቦጋለ ሴቶች በቤተሰቦቻቸውና በማህበረሰባቸው ትልቅ ክብር የሚሰጥበት፣ በቀጣይ ህይወታቸው ሙሉነት እንዲሰማቸውና እኩልነታቸው የሚያረጋግጥ በዓል ነው።

ትውልዱ ከተለያዩ መጤ ባህሎችን ተጠብቆ በማህበረሰቡ ዉስጥ ያሉ እሴቶችን የማስቀጠል ስራ ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።

ይህንን በዓል በላቀ ደረጃ ከፍ በማድረግ በሀገሪቷ በሁሉም አከባቢዎች እንዲከበር ከማድረግ ባለፈ የጉራጌ እናቶች በዓል አንትሮሽት በአለም ደረጃ ለማስተዋወቅ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ እንዳሉት የአንትሮሽት በዓል ቀን እናቶች የሚመሰገኑበትና የሚከበሩበት እሴት ወደ አንድ በማምጣት በቀጣይ በሁሉም የሀገሪቷ ክፍል ወጥነት ባለው መልኩ በማክበር የቱሪዝም ሀብት እንዲሆን ይሰራል።

የሌላውን አለም መጤ ባህል ከመከተል ይልቅ ያሉንን እምቅ ሀገር በቀል ሀብቶቻችንን በተገቢው መጠቀም ይኖርብናል ብለዋል።

ይህ በዓል በቀጣይ በአደባባይ ከማክበር ባለፈ ሀገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን አለም አቀፍ በማድረግና የባለቤትነት መብት በማረጋገጥ በዩኔስኮ የቅርስ መዝገብ ለማስመዝገብ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአንትሮሽት በዓል ተቀዛቅዞና ጠፍቶ ከነበረበት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በጥናትና ምርምር በማስደገፍ ዛሬ በአደባባይ እንዲከበር ላደረጉ ለወልቂጤ ዩንቨርሲቲ ምሁራንና በዓሉ በደመቀ መልኩ እንዲከበር ላደረጉ አካላት አመስግነዋል።

የቸሃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ሽምንሳ በበኩላቸው አንትሮሽት ለሰላም፣ ለማህበራዊ፣ ለፖለቲካዊና ለኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በመረዳት በዓሉ በሀገር ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ መሰራት ይኖርበታል።

የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ተመስገን ገብረመድህን የአንትሮሽት ባህላዊ ቱፊቱን ጠብቆ በሀገር ደረጃ ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች በማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸው ለዚህም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል።

የወልቂጤ ዩንቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሀብቴ ዱላ የወልቂጤ ዩንቨርሲቲ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ሀገር በቀል እውቀቶችና ባህል ልማት ላይ የጥናትና ምርምር ስራዎች በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በዚህም ውስጥ አንትሮሽት አንዱ ነው ብለዋል።

ይህ የአንትሮሽትና ሌሎችም መሰል ባህሎቻችንን ለማስተዋወቅና ለትውልድ ለማስተላለፍ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የበዓሉ ተሳታፊ እናቶች በጋራ በሰጡት አስተያየት ተቀዛቅዞ የነበረውና በመጥፋት ላይ የሚገኘው የአንትሮሽት በዓል የዞኑ መንግስት ትኩረት በመስጠት በዞን አቀፍ ደረጃ እንዲከበር በማድረጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ይህ በዓል እንዳይጠፋና ቀጣይነት እንዲኖረው ብሎም እንዲተዋወቅ መሰራት እንዳለበት ጠቁመው የእናቶች የምስጋና ቀን በደመቀ መልኩ እንዲከበር ላደረጉ አካላት አመስግነዋል።
በአሉ በደመቀና ባማረ መልኩ እንዲከበር ላደረጉ አካላት እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የቀጣይ የአንትሮሽት በዓል አዘጋጅ የጉመር ወረዳ መሆኑንም ተረጋግጧል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN
ቲዊተር- https://4pvf.short.gy/bTJNNn

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *