አርቲስት ጸጋዬ ሲሜ በቡኢ ከተማ የገነባው “ኦሴባሳ ጥላ” ሆቴል በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

መስከረም 28/2014 ዓ.ም

አርቲስት ጸጋዬ ሲሜ በቡኢ ከተማ የገነባው “ኦሴባሳ ጥላ” ሆቴል በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

አርቲስቱ በጥበብ ሥራው የማህበረሰቡን ባህል ከማስተዋወቁ ባለፈ በአካባቢው ልማት ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተገለጸ።

የከተማ አስተዳደሩ አርቲስቱ በአካባቢው ልማት ላይ እያበረከተ ለሚገኝው አስተዋጽዖ ለፕሮጀክቱ ማስፋፊያ የሚሆን 3 መቶ ካሬ ሜትር ቦታ እንደሚያበረክትለት ገልጸዋል።

ሌሎችም የአካባቢው ተወላጆች እና ባለሀብቶች ወደ አካባቢው መጥተው ማልማት ቢፈልጉ እንደ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ገልጸዋል።

በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ የፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ እጸገነት መንግስቱ አርቲስቱ የጉራጌ ማህበረሰብ በተለይም የሶዶ ክስታኔ ቋንቋ፣ ባህል እና ወግ በማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከተ ድንቅ የህዝብ ልጅ ነው ብለዋል።

አርቲስት ጸጋዬ ሀገራችን የውጭም ሆነ የውስጥ ጠላቶቿዋ ጦርነት ባወጁባት ጊዜ እንደ ሀገር መንግስት ጥሪ ሲያስተላልፍ በሙያው የመከላከያ ሠራዊታችንን በማጀገን ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቶዋል ብለዋል።

አርቲስት ጸጋዬ ከአርቱ በተጨማሪ እያበረከተ ያለው አስተዋጽዖ የላቀ እንደሆነ እና ለሌሎችም አርዓያ እንደሆነ ተናግረዋል።

አካባቢው ከአዲስ አበባ ካላው ቅርበት አንጻር በተለይም በሆቴል ቱሪዝም ዘርፍ ብዙ የመልማት አቅም ያለው አካባቢ ስለሆነ ሌሎችም ተወላጅ ባለሀብቶች እንደ ጸጋዬ ኢንቨስት በማድረግ አካባቢውን ለማልማት መሥራ ያስፈልጋል ብለዋል።

የሶዶ ክስታኔ ሶስቱም መዋቅሮች አርቲስቱን ለማበረታታት አንድ አንድ ሰንጋ ያበረከቱለት ሲሆን የቡኢ ከተማ አስተዳደር የዋንጫ እና የእውቅና የምስክር ወረቀት አበርክቶለታል።

አርቲስት ጽጋዬ ሲሜ በሥራው ላገዙት ላበረታቱት አካላት እና ለመላው የሶዶ ክስታኔ ማህበረሰብ በተለይም ለቡኢ ከተማ ወጣቶች ልባዊ ምስጋናውን አቅርቧል ሲል የዘገበው የቡኢ ከተማ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *