አረፋ በወልቂጤ

ሰኔ 18/2O15 ዓ/ም

አረፋ በወልቂጤ

አረፋ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ የዞኑ ህዝቦች በተለያየ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ከሚኖሩበት የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ትውልድ ቀዬአቸው የሚመለሱበትና በዓሉን፣ ከቤተሰብ፣ ከዘመድ አዝማድ፣ ከአብሮ አደግ ጓደኛ ወ.ዘ.ተ ጋር በመሆን የሚያከብሩት ታላቅ በዓል ነው።

የአረፋ በዓል በስራ ምክንያት ተራርቆ የቆየውን ዘመድ አዝማድ ከያሉበት አስባስቦ የሚያገናኝ በዓል ሲሆን በወልቂጤ ከተማ አስተዳደርም በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት በድምቀት የሚከበር በአል ነው፡፡

ለበዓሉ ማድመቂያነትም የተለያዩ ዝግጅቶች ይደረጋሉ።
ከዚህም የእናቶች ዝግጅት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።

እናቶች ቆጮ ከመፋቅ እስከ መጋገር፣ ቅቤ በማዘጋጀትና ሚጥሚጣ በመውቀጥ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሲሰሩ ሴት ልጃ ገረዶች ደግሞ የመኖሪያ ቤቶችን በማስዋብ፣ የመመገቢያ ቁሶችን በማፅዳት፣ የቤተሰቡን አልባሳት ሁሉ በማጠብና ሌሎች ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁናቴዎችን በሚያሟሉ ስራዎች ላይ ይጠመዳሉ፡፡

ልክ እንደ ሴቶቹ ሁሉ ለአረፋ በአል ወንዶቹም ሃላፊነት አለባቸው። በዋናነት ለበዓሉ የሚሆን የማገዶ እንጨት ፈልጦ በማድረቅና ቆጥ ላይ በመስቀል፣ ለእርድ የሚሆን ከብት ገዝቶ የማቅረብ ተግባር ያከናውናሉ።

በተለይ ወልቂጤ ከተማ የዞኑ ዋና መቀመጫ እንደ መሆኑ በአረፋና በመስቀል በዓል ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ሲጓዙ ያርፉበታል። ታዲያ በሚያስገርም ሁኔታ በመኪና ተከታትለው ሲገቡ ድንቅ ከመሆኑም ባለፈ በዓለም መዝገብ ሊካተት የሚችል ጉዳይ ነው፡፡

የአረፋ በዓል ቀደም ሲል ተጫጭተው የቆዩ የሚሞሸሩበት፣ ሌሎች ትዳር ለመመስረት የትዳር ጓደኛቸውን የሚመርጡበትና በባህሉ መሠረት የሚታጩበትም ጭምር መሆኑን አባቶች ያስረዳሉ፡፡

የተቀያየሙ ባልና ሚስት፣ ልጅና ወላጅ፣ ጎረቤታሞች ወ.ዘ.ተ በአረፋ ሰሞን ‹‹ይቅር›› ተባብለው ሠላምን የሚያወርዱበት ሌላኛው የአረፋ በዓል ማህበራዊ ፋይዳ ነው። ለበዓሉ የተዘጋጀውን አብረው በመብላትና በመጠጣት ይደሰታሉ፡፡

በሙስሊም ማህበረሰብ ዘንድ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበረው የአረፋ በአል በበዓሉ የተለያዩ ክንውኖችም ይካሄዳሉ። ከነዚህም የሴቶች አረፋ አንዱ ነው፡፡ የሴቶች አረፋ ከዋናው አረፋ በዓል በዋዜማው የሚከበር በዓል ሲሆን በዚህ ዕለት ሴቶች የበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የሚያረጋግጡበት ቀን ነው፡፡

በዚሁ እለት ሴቶች የጎመን ክትፎ እና ዝማሙጃት በማዘጋጀት እንዲሁም የቅቤ ቡና በማፍላት ቤተ-ዘመድና ጎረቤት ጠርተው በፍቅር የሚገባበዙበትና የሚደሰቱበት እለት ነው፡፡

የእስልምና እምነት ተከታዮች በአረፋ በዓል የሚያከናውኑት ሌላኛው ተግባር የእርድ ስነ-ስርዓት ነው። በእስልምና ህግ አንድ ሰው ካረደ ኡዱሁያ ያወጣል። ይህም በአካባቢው ለሚገኙ አቅመ ደካማ ለሆኑ [ድሆችን] አካፍሎ እንዲጠቀም ሃይማኖቱ ያዛል፡፡

የአረፋ በዓል ከሚፈጥረው ማህበራዊ መስተጋብር፤ ከሚኖረው መልካም ግንኙነት እንዲሁም የዝምድና ትስስር መጠናከር አንፃር ሲታይ እየፈካና እያበበ የሚሄድ ሲሆን በተለይ ዛሬ ዛሬ ለጭስ አልባው ኢንዱስትሪ [ቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚ እድገት ትልቁን ስፍራ በመያዙ የቱሪስት ፍሰት በየዓመቱ በእጥፍ እንደሚጨምር በየስፍራው ከሚሰበሰቡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ይህ አኩሪ ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን በማስተዋልና በእውቀት ከተመራ ለቱሪዝም ሃብት ልማት እድገት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ነው።
መረጃው የወልቂጤ ከተማ ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *