ነቖ “የልጃገረዶች” በዓል ከጠፋበት በመታደግ በማልማትና በማስተዋወቅ በሁሉም አከባቢ እንዲከበር ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ።

ጥር 19/2015ዓ.ም

ነቖ “የልጃገረዶች” በዓል ከጠፋበት በመታደግ በማልማትና በማስተዋወቅ በሁሉም አከባቢ እንዲከበር ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ።

ለረጅም ጊዜ ተቀዛቅዞ የነበረውን ነቖ “የልጃገረዶች” ቀን በዓል በወልቂጤ ከተማ አዘጋጅነት በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

ነቖ (ኧረቘ) በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ በጥር ወር ላይ ወይም ገና በዋለ እስከ 15ኛው ቀን ባሉት ጊዜያት በሴት ልጃገረዶች የሚዘወተር ባህላዊ የጨዋታ አይነት ነው።

የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ተመስገን ገብረመድህን በበዓሉ እለት ተገኝተው እንዳሉት ነቖ “የልጃገረዶች” በዓል ከ15- 20 ለሚያህል ቀናት የሚጫወቱት በመሆኑ ሴት ልጃ ገረዶች ነጻነታቸውን የሚያውጁበትና ደስታቸውን የሚገልጹበት በዓል ነው።

በበዓሉ ወቅት ልጃገረዶች ተሰባስበው በየቤቱ እየዞሩ ልክ እንደ አበባዮሽ በአይነትና ገንዘብ ይሰበስባሉ፣ ሁሉም የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችና ምግብ ከተዘጋጀ በኋላ ከአካባቢው በአንዷ ልጃገረድ ቤት በማደር የተለያዩ ምግቦችን በማዘጋጀት እየጨፈሩና እየበሉ ያድራሉ፡፡

በጉራጌ ብሔር በርካታ ባህላዊ እሴቶች መኖራቸውን ገልጸው ግሎባላይዜሽ ባሳደረው ጫና ምክንያት እየደበዘዙና በመጥፋት ላይ የሚገኙ መኖራቸዉና እነዚህም ልንታደጋቸው ይገባል።

አንትሮሽ የእናቶች ቀን ዞን አቀፍ በዓል በትላንትናው እለት በአደባባይ መከበሩን አስታውሰው ነቖ “የልጃገረዶች” በዓል ከጠፋበት እንዲያንሰራራ ለማድረግ የተጀመረውን ስራ በቀጣይ በሁሉም አከባቢዎች ለማስፋት እንደሚሰራም አመላክተዋል።

በቀጣይ ይህ ቀን በሁሉም አከባቢ እንዲከበር ከማድረግ ባለፈ በማልማትና በማስተዋወቅ ከፍ ብሎ እንዲከበር ለማድረግ ሁሉም ርብርብር ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እጸገነት ፍቃዱ በበኩላቸው የጉራጌ ብሔር አለም ባልሰነጠነበት ወቅት እንኳ ለሴቶች መብት ነጻነት ምን ያህል ይሰጥ እንደነበር የአንትሮሸትና የነቖ በዓል ማሳያ ናቸው ብለዋል።

የነቖ በዓል በጥር ወር የሚከበር ሲሆን ከታህሳስ ወር ጀምሮ ለበዓሉ የሚሆን ቅድመ ዝግጅት እንደሚጀመር ገልጸው ክትፎ፣ ቆሎ፣ በሶ፣ ቦርዴና ሌሎችም ባህላዊ ምግቦች ዝግጅቶች እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ልጃገረዶቹ ከሚያደርጉት ዝግጅት ባለፈ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ወላጆቻቸው አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርጉላቸውም ጠቁመዋል።

በዓሉ ከጠፋበት ለመታደግ የወልቂጤ ዩንቨርሲቲ ምሁራን በዘርፉ በቂ ጥናትና ምርምር ማድረግ እንዳለባቸው አመላክተው በቀጣይ ይህ ቀን የአደባባይ በዓል ሆኖ እንዲከበር መሰራት ይኖርበታል ብለዋል።

የበዓሉ ተሳታፊ ልጃገረዶች በጋራ በሰጠት አስተያየት በመጥፋት ላይ የሚገኘው ነቖ የልጃገረዶች በዓል በዚህ ደረጃ መከበሩ መደሰታቸውን ገልጸው በዓሉ ቀጣይነት እንዲኖረው መሰራት ይኖርበታል።

የተሰበሰበው የጥራጥሬ አይነት ገብስና ሌሎችም ገበያ ወስደው በመሸጥ ብሩን ጌጣጌጥና የተለያዩ ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ይገዙበታል።

ነቖ ሴት ልጃገረዶች ነጻነታቸውን የሚያውጁበት፣ ፍላጎታቸውን የሚገልጹበት በዓል መሆኑን አንስተው በዓሉ ወር ሲቀረው ጀምሮ ቅደመ ዝግጅት ይደራጋል ብለው በበዓሉም ቤት ለቤት እየተዞረ ብርና በአይነት እንደ ገብስ፣ አተር ይሰጣቸዋል።

ከዚህም ባለፈ ታላላቆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ለበዓሉ የሚሆኑ እንደ አይብ፣ ክትፎ፣ ቆሎና በሶ አዘጋጅተውላቸው እየተመገቡ ያከብሩታል።

በዓሉ በሌሎች ብሔረሰብ እንደሚከበሩ በዓላት የአደባባይ በዓል እንዲሆን እውቅና መስጠትና መተዋወቅ እንዳለበት አስታውቀዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN
ቲዊተር- https://4pvf.short.gy/bTJNNn

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *