ትምህርት ቤቶች የማህበረሰቡ እንደመሆናቸው ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጡ ሁሉም ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም አስታወቁ።

ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ዘመናዊ ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተሮች በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ጉብሬ ክፍለ ከተማ ለሚገኘው ለአባ ፍሯንሷ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ድጋፍ አድርገዋል።

ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ጉብሬ ክፍለ ከተማ አባ ፍሯንሷ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተገኝተው ድጋፍ ባበረከቱበት ወቅት እንዳሉት ትምህርት ቤቶች የትውልድ መቅረጫ እንደመሆናቸው መጠናከር ይኖርባቸዋል።

ለሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ አስተዋጽኦ ካደረጉ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ስለመሆናቸው የሚገልፀው ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም የአባ ፍሯንሷ ትምህርት ቤት እንዲቆረቆርም የመስሪያ ቦታ ከመስጠት ጀምሮ በቁስና በጉልበት በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ አኑረዋል።

በዚህም ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ባመሩ ቁጥር ትምህርት ቤቱ ሳይጎበኙ እንደማይሄዱ የገለፁት ብርጋዴር ጄኔራሉ ትምህርት ቤቱ ብዙ የዕውቀት ባለቤት የሆኑ ወጣቶች የሚፈሩበት እንደሆነ በዋናነት ትምህርት ቤቶች የማህበረሰቡ እንደመሆናቸው ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጡ ሁሉም ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ጡረተኛ ቢሆኑም በትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የሚማሩባቸው በቂ ኮምፒዩተር አለመኖሩን ያሳሰባቸው ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ልጆቻቸውን በማስተባበር ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ዘመናዊ ዴስክ ቶፕ ኮምፒዩተሮችን ለትምህርት ቤቱ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

በተጨማሪም አንድ ላፕቶፕ ኮምፒዩተርና በእርሳቸው የተፃፈው “የጦር ሜዳ ውሎ” የተሰኘው መጽሐፋቸውም ለትምህርት ቤቱ በስጦታ አበርክተዋል።

በቆይታቸውም የህይወት ተሞክሯቸውን ለተማሪዎች ያካፈሉ ሲሆን ተማሪዎችም ውጤታማ ለመሆን ትምህርታቸውን በጥብቅ መከታተል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊና የከንቲባ ተወካይ ዶክተር ወልደማሪያም ዘሬ ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ትምህርት ቤቱ ከመቆርቆር ጀምሮ በሂደቱም ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጥ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ መሆኑን አስታውሰው አሁንም ተማሪዎች ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቁ ዘመናዊ ኮምፒውተሮች ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረው በዚህም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

ወቅቱ የቴክኖሎጂ እንደመሆኑና ተማሪዎችም በዘርፉ ዕውቀት እንዲኖራቸው ኮምፒውተር ወሳኝ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን በዋናነት ለተማሪዎች ብሎም ለመምህራን ያካፈሉት የህይወት ተሞክሮ ብዙ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ መንዚላት አሕመድ በበኩላቸው ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ለትምህርት ቤቱ ላደረጉት የኮምፒውተር ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት 2O ዘመናዊ ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተሮች ለትምህርት ቤቱ ድጋፍ ማድረጋቸውን የተናገሩት ሃላፊዋ ይህም በዘርፉ ያለውን የግብዓት እጥረት ይቀርፋል ብለዋል።

ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የትምህርት መሰረተ ልማት መሟላት ትልቅ ሚና ይጫወታል በማለት በተለይም የአባ ፍሯንሷ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የራሱ ገቢ የሌለው መሆኑና በማህበረሰቡ ተሳትፎ የሚተዳደር በመሆኑ በተፈለገው ልክ ግብዓት ማሟላት አልተቻለም ብለዋል ሃላፊዋ።

ትምህርት ቤቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምር ተናግረው በብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም የተደረገው የኮምፒውተር ድጋፍ ተማሪዎች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያደርግ መሆኑና ሌሎች አካላትም ይህን ልምድ በመውሰድ በትምህርት ቤቱ በየዘርፉ የሚስተዋለውን የግብዓት ችግር እንዲቀርፉ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የአባ ፍሯንሷ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ዘሪሁን ወልደሃዋሪያት የኮምፒውተር ድጋፍ ተማሪዎች ስታንዳርዱን ጠብቆ ለማስተማር የሚያስችል በመሆኑ ድጋፉን ላበረከቱት ለብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማርያም ምስጋና አቅርበዋል።

ከትምህርት መርሃ-ግብር አንዱ የአይ ሲቲ መርሃ-ግብር ነው ያሉት ርዕሰ መምህሩ ዘርፉ ሌሎች የትምህርት መርሃ-ግብር ለማሳካት የሚያስችልና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑንም ገልፀዋል።

በትምህርት ቤቱ ያነጋገርናቸው ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተማሪያም ያካፈሏቸውን የህይወት ተሞክሮ ልምድ መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም ጊዜያቸውን በተገቢው በመጠቀም ውጤታማ ለመሆን ተግተው እንደሚማሩ ተናግረዋል።

መረጃው የወልቂጤ ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *