ተስፋ ንዳ “ጉዞ ጉራጌ 3” የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ለመጎብኘት ወደ ጉራጌ ዞን ለመጡ የሚዲያ ባለሙያዎች የጉራጌ ዞን አስተዳደር አቀባበል አደረገላቸው።
በጉራጌ ዞን የሚገኙ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ሀብቶችና ሌሎች የብሄሩ እሴቶች ለአለም ህዝብ በማስተዋወቁ ረገድ የሚዲያ ባለሙያዎች የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ተገለጸ።
የጉራጌ ዞን አስተዳደር ተወካይና የባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ ለጋዜጠኞቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት የጉራጌ ብሔር የበርካታ የባህል፣ የቱሪዝም ሀብት ባለቤት መሆኑን አንስተዋል።
የጉራጌ ብሔር በአለም አቀፍ ደረጃ የፍይናንስ ተቋማት መነሻ ለመሆን ያስቻለው የእቁብና የእድር መስራች ከመሆኑም ባለፈ በአለም አቀፍ ደረጃ ስለሴት ልጅ መብት መከበር ባልተጀመረበት ወቅት አስቀድማ የሴቶች ነጻነትና መብት የተማገተችው የቃቄ ውርድወት፣ የአንትሮሸት( እናቶች ቀን) የነቆ(የልጃ ገረዶች ቀን)፣ የአረፋና መስቀል ድንቅ እሴቶች ባለቤት ነው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ የገጠር ኮሪደር መነሻ ያደረጉት የቀድሞ አባቶች ያለ ምህንድስና የተጠበቡበት የጀፎረና የአኗኗር ዘይቤ እንዲሁም የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ ፏፏቴዎች፣ የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ፣ ጥብቅ ደኖችና ሌሎችም በርካታ የቱሪዝም እሴቶች እንዳሉት ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በዞኑ የአለም ህዝብ ሊያውቃቸው፣ ሊማርባቸው እንዲሆም እንደ ሀገር ይህንን እምቅ የቱሪዝም መብቶችን በተገቢው በመጠቀም ከዘርፉ ሀገሪቷ ማግኘት ያለባትን ሀብት እንድታገኝ ጋዜጠኞች፣ አርቲስቶችና ሌሎችም የሚዲያ አካላት በማስተዋወቁ ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።
የተስፋ ቲቪና የእማት ሚዲያ ጀነራል ማናጀር አቶ ተስፋ ንዳ የጉራጌን ባህል፣ የቱሪዝም እሴቶችን በማስተዋወቁ ረገድ እያበረከተው ያለው አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ተካ በበኩላቸው ፓርኩ በጉራጌ ዞን የሚገኝ የቱሪዝም መስህብ ቢሆንም ብዙም ያልተዋወቀ እንደነበረ ገልጸዋል።
ብሔራዊ ፓርኩ በ1997 ጥናት ተደርጎበት በ2003 ዓ.ም በቀድሞ ደቡብ ክልል ጸድቆ ወደ ብሔራዊ ፓርክ መቋቋሙን አንስተዋል።
በፓርኩ ውስጥ የተለያዩ እፀዋቶች፣ 240 የተለያዩ አእዋፋቶች፣ አራዊቶች፣ የተፈጥሮ ደኖች፣ ፏፏቴዎች፣ ፍል ውሃዎችና ሌሎችም እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ይህን እምቅ ሀብት በማስተዋወቅ የቱሪዝም ሀብት እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የተስፋ ቲቪና የእማት ሚዲያ ጀነራል ማናጀር አቶ ተስፋ ንዳ እንዳሉት የጉዞ ጉራጌ አላማ በዞኑ የሚገኙ የቱሪዝም ቦታዎችን በማስተዋወቅና በነቃቃት የቱሪዝም ሀብት እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ ነው።
ከዚህ ቀደም ጉዞ ጉራጌ ለሁለተኛ ዙር መካሄዱን ያነሱት አቶ ተስፋ አረቅጥ፣ ቦዠባር፣ መስቀል ጉንችሬ፣ እምድብርና ዘቢዳር ተራራን መነሻ ያደረገ ጉዞ መደረጉንም አስታውሰዋል።
የጉራጌ ቱሪዝም ለማነቃቃትና ለማስተዋወቅ ከመላው ሀገሪቱ በሚዲያ ስራ የሚታወቁ የቱሪዝም ጋዜጠኞች፣ ኮሜድያን፣ ተዋንያኖችን፣ አርቲስቶች፣ ድምጻውያን፣ ታዋቂ ሰዎችን በማሰባሰብ ለሶስተኛ ዙር ጉዞ ጉራጌ የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክና በውስጥ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለሌሎች ለማስተዋወቅ ያለመ ጉዞ መሆኑን ተናግረዋል።