ተማሪዎች ዝንባሌያቸዉ ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በማድረግ የአካባቢዉን ማህበረሰብ ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎ በመፍጠርና በዘርፉ ዉጤታማ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ የእዣ ወረዳ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎዲ ጽህፈህ ቤት አስታወቀ።

የወረዳዉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽህፈት ቤት እና ትምህርት ጽህፈት ቤት በጋራ በመተባበር የተዘጋጀ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች ዉድድርና ኤግዚቢሽን የማጠቃለያና የፓናል የዉይይት መድረክ በአገና ከተማ ተካሄዷል።

ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የአዲሱ ትዉልድ ቋንቋ እና የሀገራችን የብልጽግና ጉዞ ድልድይ ነዉ።

የእዣ ወረዳ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሪት ረሂማ ሙህታጅ እንዳሉት በሀገራችን ትኩረት ከተደረገባቸዉ ዘርፎች መካከል በግብርና ፣በኢንዱስትሪ ፣ በማዕድን ፣በማኒፋክቸሪንግና በሌሎችም ዘርፎች ተቋሙ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በእነኚህ የትኩረት መስኮች ቴክኖሎጂን ለማዘመንና በዲጂታል ኢኮኖሚ ለማረጋጥ ተቀብሎ የሚሰራ ተቋም እንደሆነም አስታዉቀዋል።

የዘንድሮ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች ኤግዚቢሽን ለየት የሚያደርገዉ በአምስት ዘርፎች የማቅረብ ስራ የተሰራ ሲሆን እነዚህም በኮሌጁ የቀረቡ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ፣ በኢንተርፕራይዝ ፣ በመመህራንና በተማሪዎች እና በግል ተወዳዳሪዎች የቀረቡ የፈጠራ ስራዎች መኖራቸዉም ተናግረዋል።

ለዉድድር የቀረቡ የፈጠራ ስረዎች ለወረዳዉ ማህበረሰብ ችግር ፈቺና በአጭር ጊዜ ዉስጥ ገበያ ላይ ቢዉሉና ምርትና ምርታማነታቸዉ የተረጋገጡ የፈጠራ ስራዎች መሆናቸዉም ጠቁመዋል።

የትኛዉም የመልማት ፍላጎት እዉን ለማድረግ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች ተግባራዊ ለማድረግ ግድ የሚልበት ዘመን ላይ እንገኛለን ብለዉ ይህንንም ለማሳካት ሴክተሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት በርካታ ዉጤቶች ማስመዝገብ መቻሉም አብራርተዋል።

ባለፉት አመታት የተቋማቸዉን ተልዕኮ ለማሳካት የኢኮቴ መሳሪያውች የሀርድዌር እና የሶፍትዌር ጥገና በማድረግ ይወጡ የነበሩ ወጪዎችን ማዳን እንደተቻለና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክህሎት ግንዛቤ ለማሳደግ በኮምፒዉተርና ኢንተርኔት አጠቃቀም ከ8ኛ እስከ 12 ክፍል ተማሪዎችና ለሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠና መሰጠቱም ተናግረዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ የአገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ የዘመነና በቴክኖሎጂ ለመለወጥ የኦንላየን ሪጂስትሬሽን አገልግልሎት መስጠት እንደተቻለም ጠቁመዋል ።

ተማሪዎች ዝንባሌያቸዉ ወደ ሳይንስ እንዲያደርጉ በተለይም በፈጠራ ስራቸዉ ላይ ትኩረት ሰጥተዉ በመስራትና ከትምህርት ቤት ጀምረዉ በክላስተር ደረጃ ኤግዚቢሽን እንዲያካሂዱ በማድረግ ረገድ በርካታ ስራዎች መሰራቱም ገልጸዋል።

በፓተንት በቅጂና ተዛማች መብቶች ለአካባቢያዊ አእምሮዋዊ ንብረት ጥበቃ ላይ የግንዛቤና የምክር አገልግሎት በመስጠት በቅርቡ የአገና ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ዬፋ ያደረገዉ የጉራጌ እንወቅ አፕ እና የአምቾ መከስከሻ ቴክኖሎጂ በፌዴራል አእምሮዊ ንብረት ጥበቃ መሰረት ፓተንታቸዉ እንዲጠበቁ መደረጉም አስታዉሰዋል።

የወረዳዉ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተጠምቀ በርጋ እንዳሉት በተማሪዎችና በመምህራኖች የሚሰሩ የፈጠራ ስራዎች የማህበረሰቡ ችግር ፈቺ ናቸዉ።

ተማሪዎች በፈጠራ ስራዎች ላይ ከተሰማሩ ትምህርት የመቀበል አቅማቸዉ የበለጠ የሚያሳድግ እንደሆነም ተናግረዉ በፈጠራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ተማሪዎች ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ፣ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር የበለጠ በማስተሳሰር ዉጤታማ ስራ እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባም አስረድተዋል።

ተማሪዎች የፈጠራ ስራ ላይ ትኩረት በማድረግ ከዉድድር ባሻገር ክህሎቶቻቸዉን ማሳደግና በትምህርት ቤቶች ደረጃ የሳይንስና የሂሳብ ትምህርቶች ላይ መሰረታዊ ችግሮች ይፈታል ብለዉ በትምህርት ቤቶች ደረጃ የሳይንስ ክበብ ሲቋቋም የሳይንስና የሂሳብ ትምህርት ችግር እንዲፈታ እንደሆነም በደንብ መገንዘብ እንደሚገባም አመላክተዋል።

ተማሪዎች በሰሯቸዉ የፈጠራ ስራ ላይ ተወዳድረዉ አለማሸነፋቸዉ ሳይሆን በሰሩ ቁጥር አዲስ ፈጠራ እንደሰሩ ማሰብ ያስፈልጋል ያሉት ምክትል አስተዳዳሪዉ በአምና ደረጃ እንደ ወረዳ የተሻለ የፈጠራ ስራዎች ይዘዉ ለዉድድር የቀረቡና አሁንም በወረዳ ደረጃ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ኤግዚቢሽኑ ላይ የቀረቡ የፈጠራ ስራ ዉጤቶች እጅግ የሚበረታቱና አዳዲስና የማህበረሰቡ ችግር የሚቀርፉ መሆናቸዉም ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች ድጋፍ ክትትልና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ታሪኩ ንዳዉ በበኩላቸዉ የፈጠራ ስራዎችም ሴቶችም እንዲሰሩ ለማድረግ ማነሳሳት ያስፈልጋል ብለዋል።

የሳይንስና የፈጠራ ጅምር ስራዎችን የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዉ በዘርፉ የሚፈለገዉን ዉጤት እንዲመጣ ቅንጅታዊዉ ስራዉ ከመቼዉም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

የአገና ሀይስኩል የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ዳንኤል መንግስቱ እና የአገና ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል የተፈጥሮ ተማሪ አማኑኤል ኑርሰፋ በጋራ በሰጡት አስተያየት ሁለቱም ወደ 14 የፈጠራ ስራ መስራት እንደቻሉና ለዉድድርም እንዳቀረቡም ጠቁመዋል።

እየሰሩት ያለዉን አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ትምህርት ቤቱ ፣ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ጽህፈት ቤት፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ፣በግብአትና የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙና ተገቢዉን አስታየት በመስጠት ድጋፍ እንዳደረጉላቸዉም ተናግረዋል።

በወረዳ ደረጃ በተዘጋጀዉ የሳይንስና የፈጠራ ስራዎች ኤግዚቢሽን ጥሩ ልምድ የወሰዱበትና በዉድድሩም በርካታ የፈጠራ ስራዎች መቅረባቸዉም አስታዉቀዋል።

በመጨረሻም በፈጠራ ስራ ከሁሉም ትምህርት ቤቶች ከአንድ እስከ 3 የወጡ ተማሪዎች ፣መምህራንና ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ክላስተሮች የሰርተፍኬትና የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *