ተማሪዎች ከንድፈ ሀሳብ እውቀት በተጨማሪ እራሳቸውን በቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቁና አለም አቀፉ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በአጽንኦት መሰራት እንዳለበት የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋና አርጋ ገለጹ።

ሰኔ 20/2015

ተማሪዎች ከንድፈ ሀሳብ እውቀት በተጨማሪ እራሳቸውን በቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቁና አለም አቀፉ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በአጽንኦት መሰራት እንዳለበት የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋና አርጋ ገለጹ።

የምስጋና በጎ አድራጎት ድርጅት ፣ገአት ፋውንዴሽን እና የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ በጋራ በመተባበር በጉራጌ ዞን ለሚገኙ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ የሁለተኛ እና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰው ሰራሽ አስተዉሎ እና ሮቦቲከስ ቴክኖሎጂ የሚያሳድጉ ግብአት ማቅረባቸው ተገልጿል።

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋና አርጋ የምስጋና በጎ አድራጎት ድርጅት መስራች የሰው ሰራሽ አስተውሎትና የሮቦቲክስ ማሳደጊያ ቁሳቁስ ድጋፉ ባበረከቱበት ወቅት እንደገለጹት የትምህርት ተቋማት ጊዜያቸው፣ ሀብታቸውና ጉልበታቸው ለትምህርት ጥራት ማዋል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ተማሪዎች ከንድፈ ሀሳብ ትምህርት ባሻገር በፈጠራ ስራዎች ላይ ያላቸው ተሳትፎ በማሳደግ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገልጸዋል።

በጉራጌ ዞን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከንድፈ ሀሳብ ትምህርት ጎን ለጎን በተግባር የታገዘ እወቀት መስጫ ማዕከላት ለማድረግ የዞኑ ተወላጆች እያደረጉት ያለው የግብዓት አቅርቦት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል በበኩላቸው ትምህርት ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት እጅግ ዋሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ባለፉት አመታት የተከተልነው የትምህርት ስርዓት ውጤታማ ባለመሆኑ በ2014 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ያስመዘገቡት ውጤት በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በትምህርት ጥራት የገጠመን ስብራት ለመጠገን በርካታ የለዉጥ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን ለተግባራዊነቱ ባለድርሻ አካላት እርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

የመማር ማስተማር ስራዎች በመሰረታዊነት ከታች ክፍሎች ጀምሮ መሰራት እንዳለበት የገለጹት ዶክተር ፋሪስ ዩኒቨርስቲው የግብአት ድጋፍ፣ የተለያዩ ስልጠናዎች ፣የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጠ መቆየቱንና በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ በበኩላቸው በዞኑ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ዘመናዊ የሆኑ የትምህርት ቁሳቁስ ከማሟላት ረገድ ዝቅተኛ በመሆኑን የምስጋኑ ፋውንዴሽን፣ የጋአት በጎ አድራጎት ድርጅትና የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ያደረጉት ድጋፍ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ተማሪዎች በቂ እውቀትና ክህሎት ሳይኖራቸው ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይገቡ እንደነበር የገለጹት ኃላፊው ችግሮቹን በመቅረፍ ተማሪዎቹ በሀገር አቀፍ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የገአት የበጎ አድራጎት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ መቅሱድ ኸይሩ እንደተናገሩት ፋወንዴሽኑ በዞኑ የሚገኙ ህጻናት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እውቀት አዳብረው ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር እንዲቀላቀሉ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

የገዓት የበጎ አድራጎት ድርጅት ከምስጋኑ ፋውንዴሽን ጋር በመሆን ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሰው ሰራሽ አስተዉሎና ሮቦቲከስ ቴክኖሎጂ የሚያሳድጉ ግብአቶች ድጋፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ድጋፍ የተደረገው በዞኑ ለሚገኙ ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች፣ ለ10 የአንደኛ እና ለ10 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የትምህርት ባለ ድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት እነዚህ የሰው ሰራሽ አስተዉሎ እና ሮቦቲከስ ቴክኖሎጂ የሚያሳድጉ ግብአቶችን ለተማሪዎች በአግባቡ በማድረስ በጥንቃቄ እንዲጠቀሙና እውቀታቸውን እንዲያሳድጉ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።

በእለቱም የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ ብቁ፣ በራሱ የሚተማመን ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት የሚያስችሉ ግብዓት ለማሟላት የጋራ መግባቢያ ስነድ የተፈራረሙ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚገኘው እሰቴም ፖወር ጉብኝት ተካሂዷል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *