ተማሪዎች በክልል አቀፍ የ8ኛ ክፍል ፈተና የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ ከወዲሁ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማሪያም የክልል አቀፍ ሞዴል ፈተና መጀመሩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ በ2016 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች በሀገር አቀፍና በክልል አቀፍ ፈተናዎች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ እየተሰራ ይገኛል።

በዞኑ በሚገኙ 326 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ሞዴል ፈተና መስጠት መጀመሩን የተናገሩት ኃላፊው 25 ሺህ 825 ተማሪዎች ለፈተና መቀመጣቸው ገልጸዋል።

ክልሉ የ8ኛ ክፍል ሞዴል ፈተና ሲያዘጋጅ የመጀመሪያው ሲሆን በተመሳሳይ የ2016 ዓም 12ኛ ክፍል ሞዴል ፈተና ክልሉ ማዘጋጀቱ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በዞን ደረጃ ሲዘጋጅ እንደነበረ እና ክልሉ አንድ ደረጃ ከፍ ተደርጎ የተሻለ ልምድና እውቀት ባላቸው መምህራን መዘጋጀቱ ተማሪዎች ለማብቃት የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል።

ፈተናው ከኩረጃ የጸዳ ለማድረግ በፈተና ደንብና ህግ መሰረት እየተሰጠ ሲሆን በአንድ ወንበር አንድ ተማሪ እንዲቀመጥ ተደርጓል ነው ያሉት።

በመሆኑም ተማሪዎች በስነ ልቦና በማዘጋጀት በቀጣይ ወር በሚሰጠው ክልል አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በዞኑ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያ ቀን ፈተና በሰላም የተጠናቀቀ ሲሆን የመጨረሻና የሁለተኛው ቀን ፈተና በነገው እለት እንደሚሰጥ አቶ መብራቴ ገልጸዋል።

አክለውም ኃላፊው በቀጣይ 2 የትምህርት ሳምንታት የሞዴል ፈተና ጥያቄዎች በመምህራኖቻቸው የሚከለስ በመሆኑ ተማሪዎችም ሞዴል ፈተና ተፈተንን በሚል ከትምህርት ቤት ሳይቀሩ እሰከ መጨረሻው ከመምህራኖቻቸው መቆየት እንዳለባቸው አቶ መብራቴ አሳስበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *