ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ፈተና የሚያስመዘግቡት ውጤት ለማሳደግ እና የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ከጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ግዩኒቨርስቲው ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን በዞኑ የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ ተማሪዎች ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ ገብሩ በ2014 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት ለማሻሻል ዩኒቨርስቲው ከጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ተማሪዎች በ2015 የትምህርት ዘመን በሀገር አቀፍ ፈተና የሚያስመዘግቡት ውጤት ለማሳደግ ከመደበኛ የትምህርት መርሀግብር ውጪ በተመረጡ ሃያ ትምህርት ቤቶች ከዩኒቨርሲቲው መምህራን በመመደብ በተመረጡ አምስት የትምህርት አይነቶች (እንግሊዝኛ ፣ ሂሳብ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ እና ባዮሎጂ) የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መመሪያ ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ በበኩላቸው የማጠናከሪያ ትምህርቱ በ2014 ዓ.ም በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ዝቅተኛ ውጤት የተመዘገበባቸው፣ የመምህራን እጥረት ባለባቸው 20 ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ዝቅተኛ ውጤት በሚመዘገብባቸው የትምህርት ዓይነቶች ማዕከል ተደርጎ እየተሰጠ ሲሆን በማጠናከሪያ ትምህርቱ በተፈጥሮ ሳይንስ ከስድስት ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ገለፀዋል።

በየትምህርት ቤቱ የሚያስተምሩ መምህራን እና በመደበኛ ክፍለ ጊዜ የሚሰጣቸው ትምህርት ማጠናከር ለትምህርት ጥራት እና ውጤት የማይተካ ሚና ያለው በመሆኑ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ሲሰራ ቆይቷል።

ተማሪዎች በቂ እውቀት እና ክህሎት ኖሯቸው ከወዲሁ እንዲማሩ ለማስቻል፣ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ለማሳደግ እንዲሁም በሂሳብ እና እንግሊዝኛ ትምህርቶች ላይ እየተመዘገበ ያለው ዝቅተኛ ውጤት ለማሻሻል በ2015 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ፈተና ከሚወስዱ ተማሪዎች በተጨማሪ የ9፣10 እና 11ኛ ክፍል ተማሪዎች ጭምር ተጠቃሚ ያደረገ የማጠናከሪያ ትምህርት ፕሮግራም እንደሆነም አክለዋል።

ዶክተር ሀብታሙ ፀጋዬ እና መምህር ትግስቱ ግርማ በማጠናከሪያ ትምህርት ከተሳተፉ መምህራን ተጠቃሾች ሲሆኑ የማጠናከሪያ ትምህርት አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ወዲህ ተማሪዎቹ እንዲነቃቁ አድርጓቸዋል ብለዋል።
እንደ መምህራኑ ገለፃ ተማሪዎቹ ከዚህ ቀደም የነበራቸው የአጠናን ስልት በመቀየር የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የሚችሉበት ስልት እንዲከተሉ ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል ።

ተማሪዎቹ መጀመሪያ የነበራቸው የውጤታማነት ስጋት በመቅረፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መነሳሳትን ፈጥሮላቸዋል ያሉት መምህራኑ የማጠናከሪያ ትምህርት በተሠጠባቸው ትምህርት ቤቶች በ2015 ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት እንደሚመዘገብ ገልጸዋል ።

በመሆኑም ዩኒቨርስቲውና የዞኑ ትምህርት መመሪያ የተማሪዎቹ ውጤት ለማሻሻል ያደረጉላቸው ድጋፍ ፍሬያማ ለማድረግ ወላጆች፣ መምህራን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የማጠናከሪያ ትምህርት ተጠቃሚ የሆኑ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ በሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል።

እንደተማሪዎቹ ገለጻ የመምህራኑ አቀራረብ እና የትምህርት አሰጣጥ ራሳቸው እንዲያዘጋጁ አድርጓቸዋል።

ተማሪዎቹ የዞኑ ትምህርት መምሪያና ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ለደረጉላቸው ድጋፍ አመስግነው ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል ሲል የዘገበው የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *