ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ማጠናከር እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

ነሐሴ 11/2014 ዓ.ም

ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ማጠናከር እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ በ2014 በጀት አመት ከ300 በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች መማሪያ ክፍሎች በመንግስትና በህብረተሰብ ተሳትፎ መገንባታቸው ተጠቁሟል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ እንደገለፁት የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

በመሆኑም እድሜያቸው ከአምስት እስከ ስድስት አመት የሞላቸው ህጻናት አቅራቢያቸው በሚገኙ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ እየተሰራ ይገኛል።

የነገው ሀገር ተረካቢ ህጻናት ደረጃቸው በጠበቁ የመማሪያ ክፍሎች ማስተማር ይገባል ያሉት አቶ አስከብር በዞኑ ደረጃቸው የጠበቁ መማሪያ ክፍሎች ለመገንባት የተጀመሩ ስራዎች ለማጠናከር ባለሀብቶች፣ ረጂ ድርጅቶችና ማህበረሰቡ ተቀናጅተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የቸሀ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተማረ ለማ በበኩላቸው በወረዳው የተደራጀ ትምህርት ቤት የሌላቸው ቀበሌዎች ተለይተዋል። በእነዚህ ቀበሌዎች የሚገኙ ህፃናት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይርቁ ህብረተሰቡና ባለሀብቱ በማስተባበር ደረጃቸው የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተዋል ብለዋል።

በዞኑ ትምህርት መምሪያ የትምህርት ቤቶች መሻሻል ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ ሙሉጌታ ታደሰ በበኩላቸዉ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ህጻናት ማንበብና ማስላት እንዲችሉ ከፍተኛ እገዛ ያደርግላቸዋል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚሰጣቸው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ ከትምህርት ገበታ የመቅረት፣ የማቋረጥና የመድገም ምጣኔ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል። እነዚህ ደግሞ በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ችግር ይፈጥራሉ ብለዋል።

ችግሮች ለመቅረፍ በዞኑ በ2014 በጀት አመት 476 ብሎኮች ለመገንባት ታቅዶ 75 ብሎኮች ተገንብተዋል። በበጀት አመቱ የተገነቡ እነዚህ ብሎኮች 300 የመማሪያ ክፍሎች እንዳሏቸው አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል።

በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ከአካባቢው ማህበረሰብና ባለሀብቶች በተጨማሪ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ ወርልድ ቪዥንና ቃለህይወት ቤተክርስቲያንና ሌሎች ተቋማት የላቀ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸው አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል።

የዞኑ ማህበረሰብ በትምህርት ስራ ያለውን የካበተ ልምድ ተጠቅሞ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በማስፋፋትና በቁሳቁስ በማሟላት ብቃት ያለውና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለማፍራት ከመቼው ጊዜው በበለጠ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub:- https://youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36CxQ
Twitter:- https://4pvf.short.gy/bTJNNn

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *