ባለፉት ዓመታት ከዓፈር ማዳበሪያ ስርጭት እና እዳ አመላለስ ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው አሳሰቡ::

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት እና የገንዘብ አስተዳደር ላይ ትኩረት ያደረገ የውይይት መድረክ በሀላባ ዞን ቁሊቶ ከተማ ተካሔዷል

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ርዕሰ መሰተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት ከዓፈር ማዳበሪያ ስርጭት እና እዳ አመላለስ ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በክልሉ ከዓፈር ማዳበሪያ አቅርቦት፣ ስርጭት፣እና እዳ አመላለስ ላይ የተስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የተዋቀረው የጥናት ቡድን ያስቀመጠውን ምክረ ሀሳብ መነሻ በማድረግ ለውጤታማነቱ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በዘርፉ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ከለበት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ እስከ ሶስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

አመራሩ ከዓፈር ማዳበሪያ እዳ አመላለስ ጋር በተያያዘ ሙሉ ትኩረቱን ለዘርፉ በመስጠት ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት በቁርጠኝነት መስራት አለበት ብለዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ላለፉት 7 እና 8 ዓመታት የማዳበሪያ አቅርቦት፣ስርጭት እና ገንዘብ አስተዳደር ላይ የሚነሱ ጉዳዮችን በመፈተሽ የክልሉ መንግስት ግብረ ሀይል አደራጅቶ ዝርዝር ጥናት ማካሔዱን ጠቁመዋል።

ከ2006 እስከ 2015/16 የምርት ዘመን በጥናቱ ላይ በማካተት ምን ያህል የዓፈር ማዳበሪያ ቀረበ፣ምን ያህሉ ተሰራጨ፣የብድር አመላለሱ በምን ሂደት ላይ እንዳለ ለማየት ተሟክሯል ብለዋል።

ባለፉት 10 ዓመታት በክልሉ በተለያዩ መጋዘኖች ሳይሰራጭ የቀረና ጊዜ ያለፈበት የዓፈር ማዳበሪያ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ የጥናት ቡድኑ በዝርዝር መመልከቱንም አቶ ኡስማን ጠቁመዋል።

በአፈጻጸም ረገድ የተስተዋለውን ውስንነት በመቅረፍ ከዕዳ ነጻ የሆነ ክልል ለመፍጠር እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

ከቀበሌ አመራር ጀምሮ እስከ ክልል ያለው አመራር በዘርፉ እየተስተዋለ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ዝግጁነቱን ማሳየቱንም አቶ ኡስማን አስረድተዋል።

በማዳበሪያአቅርቦት፣ስርጭት እና እዳ አመላለስ ላይ ጠንካራ ተቋም በመፍጠር በአጭር ጊዜ የላቀ ለውጥ ለማስመዝገብ በውይይት መድረኩ የጋራ መግባባት ላይ ስለመደረሱም ተናግረዋል።

መረጃው የክልሉ ኮሚኒኬሽን ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *