ባለፉት አስር አመታት በተሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዳሳደገላቸው የጌታ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

መጋቢ

በ2015 ዓ.ም በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ለማልማት ከታቀደው 99ሺህ 5መቶ ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን ከ85 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት መልማቱን የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

አርሶ አደር ገብሬ አስፋው በጌታ ወረዳ የሰንና ቆረፍቻ ቀበሌ አርሶ አደር ሲሆኑ መንግስት የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያወርዳቸው ቴክኖሎዎች በመተግበራቸው ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት አስር አመታት በልማት ቡድንና በግል ማሳቸው ላይ ባከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ውሃ በማስረግ የመሬት ለምነቱ እንዲጠበቅና መሬታቸው እንዳይሸረሸር ረድቷቸዋል።

ለምነቱን የተጠበቀ ማሳ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የገለጹት አርሶአደር ገብሬ ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ የገቢ አቅማቸው እንዳሳደገላቸው ገልጸዋል።

እንደ አርሶአደር ገብሬ አስፋው ገለጻ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት አፈርና ውሃ እንዲጠበቅ ከማድረግ በተጨማሪ አርሶአደሮች የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ እድል ፈጥሮላቸዋል።

የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ የዞኑን አርሶ አደሮች የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በወል መሬትና በግል ማሳቸው ማከናወን በመቻላቸው ተጠቃሚነታቸው እያደገ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በዞኑ አርሶአደሮች ዘንድ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ከመሆን አልፎ እንደባህል ተጠባቂ ተግባር እየሆነ መጥቷል።

እንደ አቶ አበራ ገለጻ ባለፉት አመታት በተከናወኑ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ስራዎች በጎርፍ ታጥቦ የሚሄደውን ለም መሬት፣ ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ማዳን በመቻሉ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል።

በየአመቱ የሚከናወኑ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎች አፈጻጸም በመገምገም ከቁጥር ባለፈ ጥራትን መሰረት በማድረግ እየተሰራ መሆኑ ኃላፊው ገልጸዋል።

በዞኑ በ2015 ዓም በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ለማልማት ከታቀደው 99 ሺህ 5መቶ ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን ከ85 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት የለማ ሲሆን ከ593ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል ብለዋል።

የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ የተከናወነባቸው አካባቢዎች ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ ከማድረግ በተጨማሪ በስነህይወታዊ ስራ ለማጠናከር ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ መሆኑ አቶ አበራ አስረድተዋል።

የጌታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በህሩ ኸይረዲን በበኩላቸው የወረዳው አርሶ አደሮች ባለፉት አመታት ያካበቱት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ልምድ በመጠቀም የተጎዱና ከጥቅም ውጭ የነበሩ የግልና የወል መሬቶች በማልማት አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ አርሶ አደሮች የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በልማት ቡድን ተደራጅተው በመስራታቸው በእንስሳት ዝርያ መሻሻል፣ በምርጥ ዘር አጠቃቀምና ሌሎች ኑሯቸው በሚያሻሽሉ ጉዳዮች እንዲወያዩና ልምድ እንዲለዋወጡ መልካም አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል።

የጌታ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በየነ ጠንክር አርሶ አደሮች ማሳቸው በጎርፍ እንዳይታጠብ የጠረጴዛማ እርከን፣ ፋናጆና ግዳግ ስራ ከመስራት ጎን ለጎን በአሲድ የተጎዱ አካባቢዎች በመለየት በኖራ እንዲታከም ይሰራል ብለዋል።

የተፋሰስ ልማት እየተሰራባቸው የሚገኙ አካባቢዎች በምግብ ሰብል የሚሸፈኑ ሲሆን አርሶአደሮች የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እንደሚያስችላቸው አብራርተዋል።

ለምነቱ የተጠበቀ መሬት ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ መስራት ይገባል ያሉት አቶ በየነ በተፋሰስ የለሙ ቦታዎች በስነህይወት ለማጠናከርና በሰብል ለመሸፈን ወጣቶች በቁርጠኝነት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *