በ2015 ዓ.ም በመንግስትና በህብረተሰብ ተሳተፎ የተከናውኑ የመንገድ ልማት ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንሚገባ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለፁ።

በበጀት አመቱ በሁሉ አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድና በህብረተሰብ ተሳትፎ በቸሀ፣በእኖርና በአዣ ወረዳዎች የተገነቡ የመንገድ ስራዎች በዞኑ ዋና አሰተዳዳሪና በሌሎችም የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ፣ በምክር ቤቱ የኢኮኖሚ ጉዳይ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባላትና በሌሎች አካላት ተጎብኝተዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች መንግስት ከሚሰራቸው ስራዎች ጎን ለጎን ህብረተሰቡንና ባለ ሀብቱን በመንገድና በሌሎች የልማት ዘርፎች በንቃት እንዲሳተፉ እንዲያስፋፉ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መረባረብ ይገባል።

በዞኑ በተገባደደው የበጀት ዓመት በቸሃ ፣እኖርና በእዣ ወረዳዎች በመንግስትና በህብረተሰብ ተሳትፎና በገጠር ተደራሽ መንገድ ፕሮጀክት ተገንብተው የተጠናቀቁ የመንገድ ልማት ስራዎች በአርአያነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በከፍተኛ ወጪ እየተገነቡ የሚገኙ መንገዶች ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ህብረተሰቡ መንገዶቹን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አቶ ላጫ አስገንዝበዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ከድር በበኩላቸው በ2015 ዓ.ም በሁሉ አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድና በህብረተሰብ ተሳትፎ ከተገነቡ መንገዶች መካከል በቸሀ በአዣና በእኖር ወረዳ የተገነቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በዞኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ በዞኑ ምክርቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴዎች አባላትና በመምሪያው የማኔጅመንትና ሌሎችም አካላት እንዲጎበኙ መደረጉ ተሞክሮዎች ለማስፋት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት በተለያዩ ጊዜያት በገጠር ተደራሽ መንገድ ፕሮጀክት የተጀመሩ መንገዶች ግንባታቸው ለማጠናቀቅ ህብረተሰቡና ባለሀብቱ ባደረጉት ተሳትፎ ውጤተማ ስራዎች ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

በህዝቡና በአካባቢው ተወላጅ ባለሀብቶች ተሳትፎ 220 ኪ.ሜ የጠጠር መንገድ ለመገንባት ግብ ተጥሎ 250 ነጥብ 37 ኪ.ሜ መንገድ ማስገንባት መቻሉን አቶ ሙራድ ገልፀዋል፡፡

በመንግስት፣ በባለሀብቱና በህብረተሰቡ ተሳትፎ 3 መቶ ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተለያዩ የመንገዶችና ድልድዮች ግንባታ ስራዎች መከናወናቸውንና በዚህም ገደባኖ ጉታዘር ወለኔ፣ ቸሀ፣እዣና ሶዶ ወረዳዎች የተሻለ አፈፃፀም ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና የመንገድ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊና የሁሉ አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ናሆሞ ታዬ በበጀት አመት በማህበረሰብ ተሳትፎ ከ190ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 250 ኪ.ሜ መንገድ ጠጠር የማልበስ ስራ መሠራቱን ተናግረዋል።

ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ መንግስት ድጋፍ 283 ኪ.ሜ የገጠር ቀበሌ ተደራሽ መንገድ ለመገንባት ታቅዶ እስከ አሁን ከ170 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የ240 ኪ.ሜ መንገዶች ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል ብለዋል፡፡

በ2015 በጀት አመት ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ከሆኑት የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል በእኖር ወረዳ የኮሰድ-አዘክር 3 ነጥብ 94 ኪ.ሜ፣ በቸሃ ወረዳ የመገናሴ-ባካኖቴ 5 ነጥብ 91 ኪ.ሜ እና አስተፖ-አሙረ 5 ነጥብ 74 ኪ.ሜ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጠቃሾች እንደሆኑ አቶ ናሆም ገልፀዋል።

በህዝብ እና በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ 190 ሚሊዮን 891 ሺህ 335 ብር በማሰባሰብ 344 ኪ.ሜ በDC-2 እስታንዳርድ 50 በመቶ የአፈር ስራ፣ 250 ኪ.ሜ በDC-2 እስታንዳርድ 100% የጠጠር ስራ እንዲሁም 84 አነስተኛ እስራክቸር እና 7 አነስተኛ ድልድዮችን ጨምሮ 215 ኪ.ሜ መንገዶች ጥገና ተደርጎላቸዋል ብለዋል፡፡

የማህበረሰቡን የልማት ፍላጎትና አቅም በአግባቡ በመጠቀም በተሰራው ስራ የተሻለ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን ተሞክሮው በመቀመር በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች ወጥነትና ተቀራራቢነት ባለው መንገድ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

አቶ ደሱ ድንቁና አቶ ተመስጌን ኑርጋ የቸሀና የእኖር ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጸህፈት ቤት ኃላፊዎች ሲሆኑ ለብዙ ጊዜ የህብረተሰቡ የመልካም አሰተዳደር ችግር የነበሩና በሁሉአቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ፕሮጀክት ሳይጠናቀቁ የቆዩ መንገዶችን ለማጠናቀቅ በዞኑ በኩል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

በወረዳዎቹ በመንገድ ልማት የነበሩ ችግሮችን በመለየት ህበረተሰቡን በማነሳሳት፣ ባለሀብቱንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በዩራፕ የተጀመሩትን ጨምሮ በርካታ የህብረተሰቡን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

የተገነቡ መንገዶች ዘላቂ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በግንባታው የተጀመረው ተሳትፎ በእንክብካቤና በጥገና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *