በ2014 የመኸር ወቅት ከ146 ሺህ 785 በላይ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ ።

በዞኑ በመኸር ወቅት በዘር ከሚሸፈነው ማሳ ከ11 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑንም ተጠቁሟል፡፡

የግብርና ሥራ ጉልበት፣ ጊዜና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲሁም ጥረት የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡

ዘርፉን ለማዘመን መንግስት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከማቅረብ በተጨማሪ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ በማሳ ዝግጅት፣ በአፈር ማዳበሪያና በምርጥ ዘር አጠቃቀም፣ በአረምና ተባይ ቁጥጥር ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው እየሰራ ነው፡፡

የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ የመኸር ማሳ ዝግጅት አስመልክተው ለጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳች መምሪያ በሰጡት መግለጫ የአርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነትን ሚያሻሽሉ አዳዲስና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው፡፡

የአርሶ አደሩ ወጪና ጉልበት በመቀነስ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በበጀት አመቱ 29 ትራክተሮች የተገዙ ሲሆን በዞኑ የሚገኙ ባለሀብቶች ያስገቧቸውን ጨምሮ 215 ትራክተሮች እንደሚገኙ ኃላፊው አስረድተዋል።

በመሆኑም አርሶ አደሮች ከተለመደውን የአስተራረስ ዘዴ ተላቀው ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ በመጠቀም አሁናዊው የኑሮ ውድነትን ሊያረጋጋ የሚችል ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በዞኑ በዘንድሮው የመኸር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን ከታቀደው ከ146 ሺህ 785 በላይ ሄክታር መሬት ከ11 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑንም አቶ አበራ ገልፀዋል፡፡

አርሶ አደሮች ማሳቸውን በመንከባከብ፣ አረምና ተባይ በመቆጣጠርና ግብዓትን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ባለሙያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል ብለዋል።

ይህንን ግብ ስኬታማ ለማድረግ አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና አርሶ አደሮች ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ አበራ ወንድሙ መልዕክት አስተላልፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *