በ2014 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ከ103 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት እንደሚለማ የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው በተቀናጀና የተፋሰስ ልማት በእንስሳትና አሳ ሀብት እና በቡና ልማት ላይ የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሄደ።

የንቅናቄ መድረኩን የመሩት የጉራጌ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ክፍሌ ለማ እንደተናገሩት ባለፉት አመታት በዞኑ የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በምርትና ምርታማነት እድገት ላይ ከፍተኛ ውጤት አስገኝተዋል።

በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያት የተጎዱ መሬቶች በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ አገግመው የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ከማሳደግ በተጨማሪ የዞኑ የደን ሽፋን ማሳደግ ተችሏል። የጠፉ ምንጮች እንዲጎለብቱ አስችሏል ብለዋል ዋና የመንግስት ተጠሪው።

በመሆኑም የተጎዱ አካባቢዎች ማገገማቸውን ተከትሎ አርሶ አደሩ ከሰብል ልማት በተጨማሪ ዝርያቸው የተሻሻለ ከብቶች በማድለብና በማመኮት እንዲሁም የወተት ምርታማነት በማሳደግ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሎታል።

እንደ አቶ ክፍሌ ገለፃ ባለፉት ዓመታት በተፋሰስ ልማት ስራ ላይ ይስተዋሉ ከነበሩ ችግሮች መካከል በአንዳንድ አካባቢዎች የተፋሰስ ልማት ስራ የተሰራባቸው አካባቢዎች ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ አለማድረግ፣ አካላዊ ስራ ተሰርቶ በስነ ህይወት ስራ አለማጠናከ፣ የተተከሉ ችግኞች በሚፈለገው ደረጃ አለማጽደቅ ተጠቃሾች ናቸው።

ሆኖም ህብረተሰቡ በተፋሰስ ልማት ስራ ያካበተው ልምድ ተጠቅሞ በዚሁ ዓመት ማስቀጠል ይጠበቅበታል ያሉት አቶ ክፍሌ ከዚህ ቀደም የነበሩ ክፍተቶች በማረም የተሻለ ስራ ለመስራት አመራሩና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ ክፍሌ ለማ አሳስበዋል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንድሙ አበራ በበኩላቸው አካላዊ ስራ በተሰማራባቸው አካባቢዎች ዘርፈብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ዛፎች መትከል ይገባል ብለዋል።

የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አካባቢ ለመፍጠር ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ያሉት ኃላፊው ከዚህ ቀደምት የነበሩ ጥንካሬዎች በመጠቀም በዞኑ በ2014 ዓ.ም በ4መቶ 13 ንዑስ ተፋሰሶች ከ103 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች እንደሚለማ ተናግረዋል።

በዚህ ተግባር ከ590 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉ ሲሆን ስራው ለ35 ቀናት ይቆያል።
አያይዘውም ኃላፊው በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ከወትሮ በተለየ የአርሶ አደሩ ህይወት በሚቀይሩ ተግባራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ከተሳተፉ ውስጥ የጌታ ወረዳ ዋና አስተዳሰሪ አቶ ቅባቱ ተሰማ እና በቸሀ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንቁ ይርጋ ይገኙበታል።

እንደ ተሳታፊዎቹ ገለጻ አርሶ አደሮች ባለፉት አመታት በተሰሩ ስራዎች ከወረዳዎቹ ባለፈ ለሌሎች አካባቢዎች በምሳሌነት የሚጠቀሱ ውጤት አስገኝተዋል ።

ከዚህ ቀደምት ለሰውና ለእንስሳት አስጊ የነበሩ የተጎዱ አካባቢዎች አገግመው የመኖ ልማት ስራ በስፋት እየተሰራባቸው ነው። በዚህም ለወጣቶች እና ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በንብ ማነብና በመኖ ዘር ሽያጭ የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።

በመሆኑም የዘንድሮው የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የአካባቢው ስነምህዳር ታሳቢነት ያደረገ ስትራክቸር ና የሚሳተፉ ሰዎች የተለዩ ሲሆን አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች ማዘጋጀት እንደተቻለና ስራው ከወደ መሬት ባለፈ በግል ማሳዎች ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀታቸው ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።

የዞኑ የ2014 ዓም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ከጥር 24/2014 ጀምሮ ወደ ተግባር እንደሚገባ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ዘግቧል።

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *